የዘንድሮው በዓል የቁም እንስሳት ግብይት መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ የታየበት ነው ሲሉ በቤንች ሸኮ ዞን በዋቻ ገበያ የተገኙ ሸማቾች ተናገሩ

የዘንድሮው በዓል የቁም እንስሳት ግብይት መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ የታየበት ነው ሲሉ በቤንች ሸኮ ዞን በዋቻ ገበያ የተገኙ ሸማቾች ተናገሩ

ሸማቾቹ አክለውም የዘንድሮው የበዓል ገበያ ከባለፉት ጊዜያት ጋር ሲነፃፀርም ከአቅርቦት አንፃር ዕጥረት ባይኖርም በሰንጋ በሬ ላይ ከ10 እስከ 15ሺህ ብር ጭማሪ መታየቱንም ገልጸዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚገኙ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላት አንዱ በቤንች ሸኮ ዞን የሚገኘው የዋቻ ማጂ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል ነው።

ጣቢያችን በስፍራው በመገኘት ተዘዋውሮ ያነጋገርናቸው ሸማቾች የዘንድሮው የበዓል ግብይት መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ የታየበት ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በገበያው በርካታ ሰንጋ በሬ፣ በግና ፍየል እንዲሁም ላሞች ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን ከትልቅ እስከ አነስተኛ በተለያዩ ዋጋዎች ሲገበያዩ ውለዋል።

በበዓል ገበያው ሰንጋ በሬ ከፍተኛው ከ80 ሺህ እስከ 120 ሺህ ብር ድረስ እየተገበየ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

መካከለኛው እንደዚሁ ከ60 ሺህ እስከ 75 ሺህ ብር ድረስ ሲገበያዩ ዝቅተኛው የከብት ዋጋ ከ20 ጀምሮ እስከ 40 ሺህ ብር ድረስ መኖሩንም ሸማቾቹ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በገበያው የበግ ዋጋም እንደዚሁ ከ4 ሺህ ብር እስከ 14 ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑንም ነግረውናል።

የዶሮ ገበያው ሲታይ ከ700 ብር ጀምሮ እስከ አንድ ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑንም አንስተዋል።

በተለይ በገበያው የእንስሳት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ገበያተኞቹ መንግስት በአካባቢው የከብት ማድለቢያ ማዕከላት እንዲስፋፉ መስራት አለበት ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን