የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማዘመንና የውስጥ የገቢ አቅሞችን ለይቶ በመሰብሰብ ለአካባቢዉን ልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው – የሺሺንዳ ከተማ አስተዳደር የኢኮኖሚ ክላስተር ጽ/ቤት

የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማዘመንና የውስጥ የገቢ አቅሞችን ለይቶ በመሰብሰብ ለአካባቢዉን ልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው – የሺሺንዳ ከተማ አስተዳደር የኢኮኖሚ ክላስተር ጽ/ቤት

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 28/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማዘመንና የውስጥ የገቢ አቅሞችን ለይቶ በመሰብሰብ ለአካባቢዉን ልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን በካፋ ዞን የሺሺንዳ ከተማ አስተዳደር የኢኮኖሚ ክላስተር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ በ2015 በጀት ዓመት ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉም ተጠቁሟል።

የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ኃይሌ አሰፋ በ2015 ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 57 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብስብ አቅዶ ከ 67 ሚሊዮን 1 መቶ 58 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ይህም ከዕቅድ በላይ የተከናወነ ነው ያሉት ኃላፊዉ ለስኬታማነቱ ከዞኑ ገቢዎች መምሪያ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አካላት ድጋፍና ክትትል ማድረጋቸው ለስኬቱ ሚና ነበራቸው ብለዋል።

በከተማዉ የደረጃ “ሐ” ነጋዴዎችን የዕለት ገቢ ለመገመት በተደረገ ጥረት 7 መቶ 8 ነጋዴዎች ላይ ግመታ መደረጉን የገለጹት ኃላፊው በሂደቱም ከ1 መቶ በላይ አዳዲስ ነጋዴዎችን ማፍራት መቻሉንም ጠቁመዋል።

በከተማዉ ከደረጃ “ሐ” ነጋዴዎች ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ከታቀደዉ በእስካሁኑ ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ማከናወን ተችሏል ብለዋል አቶ ኃይሌ።

አሁን ላይ የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር መሰብሰብ የተጀመረ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ነጋዴዎች በጊዜ የሂሳብ መዝገባቸዉን በባለሙያ አሰርቶ በማቅረብ ግብራቸዉን እንዲከፍሉም አሳስበዋል።

ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት ከ93 ሚሊየን ብር በላይ ዕቅድ እንደያዘ የተናገሩት ኃላፊው ተቋሙ ዕቅዱን ማሳካት እንዲችል ከሰው ማሟላት ጀምሮ ተያያዥ ድጋፎች ከሚመለከታቸው አካላት ይጠበቃል ብለዋል አቶ ኃይሌ።

ዘጋቢ፡ አሰግድ ሳህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን