ለበዓል ገበያ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል – የኮንታ ዞን ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 28/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ ነጋዴዎችና ተቋማት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የኮንታ ዞን ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።

እንደ ሀገር የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ተከትሎ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዝግጅት መጠናቀቁን የዞኑ ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ኬሃሞ ተናግረዋል።

ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዲባባስ የሚያደርጉ ደላላዎችን ከገበያ የማውጣት ስራ እየተሠራ መሆኑን አቶ ንጋቱ ገልፀዋል።

በዓልን ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎችም ሆነ ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱም ጭምር ነው ኃላፊው አክለው ያሳሰቡት።

በዞኑ አመያ ከተማ ገበያ ለበዓል ሰንጋ ሲገዙ ካገኘናቸው መካከል አቶ ታጋይ ዶኖቾና ሌሎችም በሰጡን ሀሳብ የበዓል ገበያ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ደረጀ ተፈራ – ከዋካ ጣቢያችን