በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ 50 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የተለያዩ በጎ ስራዎች መከናወናቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2015 ዓ.ም ክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ 50 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የተለያዩ በጎ ስራዎች መከናወናቸውን የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል አስታወቀ፡፡

ሆስፒታሉ የክረምት በጎ ፈቃድ ማጠቃለያ ፕሮግራም ባካሄደበት ወቅት ነው ይህንን የገለፀው።

ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ልየታና ህክምና መስጠት፣ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ቀዶ ጥገናዎችን ከበጎ ፈቃደኞች ጋር በመነጋገር የማመቻቸት ስራ፣ የአንድ አቅመ ደካማ ቤተሰብ የቤት ግንባታ መደረጉና ሌሎችም በክረምቱ በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መሰጠታቸውን የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ ጋርሾ እና የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አይፎክሩ ግዛቸው በጋራ አስረድተዋል።

የደም ልገሣ፣ ህዝባዊ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የስኳር ህሙማን ልየታና ህክምና በተጨማሪነት ከተከናወኑት መካከል እንደሚጠቀሱ ተገልጿል።

በተለይ ከዞኑ አልፎ ለአጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው ህፃናት ትረስት በጎ ፈቃድ ማህበር ጋር በመቀናጀት ነፃ የቀዶ ጥገና ህክምና መሰጠቱም ተመላክቷል።

ይህ አገልግሎት ግለሰቦች ከራሳቸው ወጪ አድርገው የሚታከሙ ቢሆን በአንድ ህፃን ከ35 ሺህ እስከ 40 ሺህ ብር ወጪ ከማስወጣቱም ባለፈ ከአካባቢው ርቀው እንዲታከሙና ወረፋ ይዘው ለተጨማሪ እንግልት የሚዳርግ ስለመሆኑም በበጎ ፈቃድ የተሳተፉ አካላትና የሆስፒታሉ የሥራ ሀላፊዎች አስረድተዋል።

ለ30 ያህል ህፃናት ቀዶ ጥገና መደረግ ተችሏልም ተብሏል።

በአጠቃላይ በክረምቱ ወደ 50 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪን ማዳን መቻሉን አቶ ማቴዎስ አስረድተዋል።

በሥራው ለተሳተፉና ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናና የዕውቅና ሰርተፊኬት ተስጥቷቸዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን