ሆስፒታሉ የሚሠጠው አግልግሎት እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሀሴ 26/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን የሣውላ አጠቃላይ ሆስፒታል በ2015 በጀት ዓመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት አፈፃፀምና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሊቃውንት አዛዜ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ167 ሺ በላይ ተመላላሽ ህክምና መስጠቱን ተናግረዋል። 939 ታካሚዎች ደግሞ ወደ ሌሎች ከፍተኛ የህክምና ተቋማት ተልከዋል ብለዋል።

አቶ ሊቃውንት አክለውም 5 ሺ 322 የድንገተኛ ህክምና መሰጠቱን ጠቅሰው ከ1ሺ በላይ ህሙማንን ከሌሎች የጤና ተቋማት በሪፈር ተቀብሎ አገልግሎት መስጠቱን አንስተዋል።

በሆስፒታሉ 2 ሺ 65 እናቶች የወሊድ አገልግሎት ማግኘታቸውን የተናገሩት ስራ አስኪያጁ 9 ሺ 872 የማህጸንና ጽንስ ህክምና መደረጉንም ገልጸዋል።

ለ144 የኮሌራ ህሙማን የህክምና አገልግሎት መሰጠቱን አቶ ሊቃውንት ጠቅሰዋል።

የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማኖቴ በበኩላቸው መምሪያው በሆስፒታሉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እያደረገ ያለውን የበጀትና የቴክኒክ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አክለውም በተያዘው በጀት ዓመት በሆስፒታሉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው ሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጡን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የዞኑ አስተዳደር ለሆስፒታሉ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በሆስፒታሉ የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው በቀጣይም በመድሀኒት አቅርቦት የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የደም ባንክ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ጠይቀዋል።

ሆስፒታሉ ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ለዞኑ እና አጎራባች ለሚገኙ ሕዝቦች የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በሆስፒታሉ የሚገኙ የህፃናት ፅኑ ህክምና ማዕከል፣ የሣውላ አጠቃላይ ሆስፒታል ሞደል ማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ እና ግንባታው እየተጠናቀቀ የሚገኘውን የሣውላ ደም ባንክ ህንፃን የውይይቱ ተሳታፊዎች ጎብኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን- ከሳውላ ጣቢያችን