የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸዉን ይበልጥ በማሳደግ ጤናዉ የተጠበቀ አምራች ዜጋን ለመፍጠር የሚያደርገዉን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ገለፀ

የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸዉን ይበልጥ በማሳደግ ጤናዉ የተጠበቀ አምራች ዜጋን ለመፍጠር የሚያደርገዉን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ገለፀ

በልዩ ወረዳው በአልቢር ሀሰን ዑንጃሞ ጤና ጣቢያ በ3.7 ሚሊየን ብር የእናቶችና ህፃናት ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተመርቋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኑ ሻቡዲን በዚህ ወቅት እንደገለፁት የአልቢር ሀሰን ዑንጃሞ ጤና ጣቢያ ከተቋቋመ ወዲህ የህብረተሰብ አገልግሎት አሰጣጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።

አልቢር የልማትና ትብብር ማህበር ከአዋሽ ባንክ አክስዮን ማህበር ጋር በመተባበር በ3.7 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባዉ የእናቶችና ህፃናት ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል በዘርፉ የተሻሉ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚረዳም ገልፀዋል።

የአልቢር ልማትና ትብብር ማህበር ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሼህ ሱልጣን ሀጅ አማን በበኩላቸዉ ልማት ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 18 አመታት በጤና፣ በትምህርት፣ በንፁህ መጠጥ ዉሃና አቅመ ደካሞችን በመርዳት በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ልማት ማህበሩ በልዩ ወረዳው የአልቢር ሀሰን ዑንጃሞ ጤና ተቋምን ከማቋቋም ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን የገለፁት ሼህ ሱልጣን ጤና ጣቢያዉን ወደ ሆስፒታል በማሳደግ የአገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ ለማድረግ ይሰራልም ብለዋል።

የአዋሽ ባንክ አክስዮን ማህበር ተወካይ አቶ ሳምሶን ሁሴን በበኩላቸዉ የአዋሽ ባንክ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቷ በተለያዩ አከባቢዎች የበጎ አድራጎት ስራዎችን በመስራት ግንባር ቀደም መሆኑን በመግለፅ በአልቢር ሀሰን ዑንጃሞ ጤና ጣቢያ በተገነባዉ የእናቶችና ህፃናት ህክምና ማዕከል 70 በመቶ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

የልዩ ወረዳዉ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብድራሂም ሙዴ በምርቃቱ ወቅት እንደገለፁት የጤና ተቋማት ያሉበትን ደረጃ በማሻሻል የህብረተሰቡን ጤና በይበልጥ ለመጠበቅ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ወይዘሮ ሰፊና ሀጅ አማንና ዙልፋ ንዳ በፕሮግራሙ ወቅት አግኝተን ካነጋገርናቸዉ ተሳታፊዎች መካከል ይገኙበታል። በጤና ተቋሙ የእናቶች የህክምና ማዕከል መገንባቱ እንዳስደሰታቸዉ ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን