በጉራጌ ዞን በሁለት ወረዳዎች የተከሰዉን የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት እየተደረገ ያለው ጥረት ህብረተሰቡ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል – የዞኑ ጤና መምሪያ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 10/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዞኑ በሁለት ወረዳዎች የተከሰዉን የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት አየተደረገ ያለው ጥረት ህብረተሰቡ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አሳሰበ፡፡
በወረርሽኙ እስካሁን በዞኑ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ሁለት ወረዳዎች 5 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።
የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሰለሞን ጉግሳ ለጣቢያችን በሰጡት መግለጫ አንደገለፁት በዞኑ በአበሽጌና በሶዶ ወረዳዎች የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ተከስቷል።
ወረርሽኙ በአበሸጌ ወረዳ ቦረር ቀበሌ በሼህ መሀመድ አወል እርሻ ልማት ካምፕ 148 የቀን ሰራተኞች በበሽታው ተጠቂ መሆናቸውንና በዚህም የ4 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተናግረዋል።
በተመሳሳይም በዞኑ በሶዶ ወረዳ ኧሽገዲየ ቀበሌ በአንድ ጸበል ቦታ 44 ሰዎች በወረርሽኙ ተይዘዉ ህክምና ላይ እንደሚገኙና እስካሁን የ1 ሰው ህይወት ማለፋን ነው ያስረዱት።
የኮሌራ በሽታ በባክቴሪያ አማካይነት ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍና መንስኤና መተላለፊያ መንገዶቹን ያብራሩት አቶ ሰለሞን በዞኑ አሁን ላይ ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ በመሆኑ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ግብረሀይል ተቋቁሞ የተጠናከረ ሥራ አየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ወረርሽኙ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት አየተደረገ የሚገኘው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የገለፁት አቶ ሰለሞን የዞኑ አስተዳደር ለህክምና ግብዓት ግዢ የሚውል የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም በመግለጫቸው አንስተዋል።
አሁን ላይ በወረርሽኙ መከላከል ዙሪያ ለህብረተሰቡ በየደረጃው ግንዛቤ አየተፈጠረ እንደሚገኝ ጠቅሰው ህብረተሰቡ በወረርሽኙ ዙሪያ ከጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ ምክረ ሀሳቦችን በመተግበር ራሱን ከወረርሽኙ መጠበቅ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።
በዞኑ የወረርሽኙ ሥርጭት እየጨመረ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሀላፊው ወረርሽኙን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ በተለይም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ለማስቀረት የቅድመ ማህጸን በር ካንሰርንና ከቅድመ ወሊድ እስከ ድህረ ወሊድ ያሉትን ምርመራዎች ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የአርባምንጭ ደምና ህብረህዋስ ባንክ በ2017 በጀት አመት ከ6 ሺህ 378 ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ
ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሰራ ነው – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት