ማህበረሰብ አቀፍ የመድኃኒት እደላ ዘመቻ በዞኑ 6 ወረዳዎችና 2 የከተማ አስተዳደሮች መጀመሩን የሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 18/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የፀረ-አንጀት ጥገኛ ትላትልና ብልሃርዝያ መከላከያ ማህበረሰብ አቀፍ የመድኃኒት እደላ ዘመቻ በዞኑ 6 ወረዳዎችና 2 የከተማ አስተዳደሮች መጀመሩን የሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል።
ለዘመቻው ስኬታማነት የጤና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
ከሐምሌ 17 እስከ 23/2015 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ይካሄዳል።
ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ አካባቢ በሽታዎች በኢትዮጵያ ከ90 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያጠቁ በመሆኑ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል የተቀናጀ ፀረ-አንጀት ጥገኛ ትላትልና ብልሃርዝያ መከላከል ማህበረሰብ አቀፍ የመድኃኒት እደላ ዘመቻ መጀመሩን በሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ በሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ቸርነት ሳዎሬ ገልፀዋል።
በሀዲያ ዞን ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በበሽታው እንደሚጠቃ የገለጹት አቶ ቸርነት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የጤና ባለሙያውንና ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የመድኃኒት እደላ ዘመቻ ለ7 ተከታታይ ቀናት የሚሰጡ መሆኑን አሳውቀዋል።
በሽታው በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ያሉት አስተባባሪው ከ5 እሰከ 19 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህፃናትንና ከ15 እስከ 49 ዓመትና በመውለድ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እናቶች የመድኃኒት እደላው ዘመቻ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አመላክተዋል።
በዘመቻው ለእናቶችና ለህፃናት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የተናገሩት አቶ ቸርነት የወረዳና የከተማ አስተዳዳሪዎችና እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና መላው ህብረተሰብ ለስኬታማነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል።
በዘመቻው በሚደረገው የመድኃኒት እደላ ወቅት ተጠቃሚዎች ንጹህ ዉሃ ይዘው መቅረብ እንደሚገባና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክረሀሳብ ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን አስከፊነት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ሊያግዙ ይገባል ብለዋል አስተባባሪው።
በዘመቻው ተሳታፊ የጤና ባለሙያዎች በሂደቱ በሚደረገው የመድኃኒት እደላ በንቃት በመሳተፍ ለህብረተሰቡ ጤና መጎልበት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በዘመቻውም ከ6 መቶ 40 በላይ የጤና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉም ተገልጿል።
ዘጋቢ: ጡሚሶ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በዚህ ዓመት 137 ቋሚና 452 ጊዜያዊ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በየደረጃው ባሉ የጤና ልማት ሰራዊት አማካኝነት ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችና የአቤትና አኳቲን ኬሚካል ርጭት ስራ መሰራቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ
በኮሬ ዞን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው – የዞኑ ጤና ዩኒት
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግርና መዘናጋት በዞኑ የወባ በሽታ እንዲጨምር ማድረጉን የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ