ሪያል ማድሪድ ያን ዲዮማንዴን በታሪካዊ የዝውውር ክፍያ አስፈረመ

ሪያል ማድሪድ ያን ዲዮማንዴን በታሪካዊ የዝውውር ክፍያ አስፈረመ

የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ የ19 ዓመቱን አይቮሪ ኮስታዊውን የፊት መስመር ተጫዋች ያን ዲዮማንዴን ከጀርመኑ አርቢ ሌይፕዚግ በይፋ አስፈርሟል።

ለዝውውሩ እስከ 140 ሚሊዮን ዩሮ የሚደርስ ክፍያ የፈፀመ ሲሆን፣ ይህም ተጫዋቹን በክለቡ ታሪክ ውዱ ፈራሚ አድርጎታል።

በአዲሱ አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ ስር ስድስተኛው የክረምቱ ፈራሚ የሆነው ዲዮማንዴ፣ በሳንቲያጎ በርናቤው ለሰባት ዓመታት የሚያቆየውን ረጅም ጊዜ ኮንትራት ተፈራርሟል።

ይህ የዝውውር ዋጋ ክለቡ በ2023 ጁድ ቤሊንግሃምን ከቦሩሲያዶርትሙንድ ለማስፈረም ከከፈለበት 133.9 ሚሊዮን ዩሮ የሚበልጥ ሆኗል።

ወጣቱን ኮከብ ለማስፈረም የፈረንሳዩ ፒኤስጂ እና የእንግሊዙ ሊቨርፑል ብርቱ ፉክክር አድርገው ነበር።

ፒኤስጂ ያቀረበው 102.5 ሚሊዮን ፓውንድ ውድቅ መደረጉን ተከተሎ ከፉክክሩ ሲወጣ፣ ሊቨርፑል ደግሞ ከክለቡ ለለቀቀው መሐመድ ሳላህ ምትክ ለማድረግ በሰኔ ወር ያቀረበው 69 ሚሊዮን ፓውንድ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

ዲዮማንዴ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በቡንደስሊጋው 12 ግቦችን በማስቆጠር እና 8 ግቦች እንዲቆጠሩ አመቻችቶ በማቀበል የውድድር ዓመቱ ኮከብ ወጣት ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል።

ከአይቮሪ ኮስት ወደ አሜሪካ አካዳሚ ያቀናው ዲዮማንዴ፣ በ2025 ወደ ስፔኑ ሌጋኔስ በመቀላቀል፣ በመቀጠልም በዚያው ዓመት ወደ አርቢ ሌይፕዚግ በመዘዋወር ፈጣን የእድገት ደረጃዎችን አሳይቷል።

ሪያል ማድሪድ በድጋሚ ሆዜ ሞሪንሆ ከቀጠረ በኋላ ስብስቡን በማጠናከር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ዲዮማንዴ ቀደም ብለው ክለቡን ከተቀላቀሉትከ በርናርዶ ሲልቫ፣ ኢብራሂማ ኮናቴ፣ ዴንዜል ዱምፍሪስ፣ ማርክ ኩኩሬያ እና ካርሎስ ኤስፒን በመቀጠል ስድስተኛው አዲስ ፈራሚ ሆኗል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ