ኒው ዳውሮ ፋውንዴሽን ከ600 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አበረከተ

ኒው ዳውሮ ፋውንዴሽን ከ600 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አበረከተ

ኒው ዳውሮ ፋውንዴሽን የበጎ አድራጎት ማህበር ከ600 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አበርክቷል።

‎በዕለቱ የ”ኒው ዳውሮ ፋውንዴሽን” 5ኛ ዓመት ክብረ በዓል በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ተካሂዷል።

‎በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አባተ ኡቃ፤ በጎ አድራጎት በማከናወን ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ በርካታ ተግባራትን ማሳካት እንደሚቻል አንስተዋል፡፡

‎የተሰበሰቡት የትምህርት ቁሳቁሶች በእጥረት ምክንያት ህፃናት ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ የሚያግዙ መሆናቸውን ገልፀው፤ ”ኒው ዳውሮ ፋውንዴሽን” እና በሂደቱ የተሳተፉ አካላትን አመስግነዋል።

‎በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ሳቢያ ተማሪዎች ከትምህርት እንዳይቀሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

‎የ”ኒው ዳውሮ ፋውንዴሽን” መስራችና ባለቤት አቶ በሀይሉ ማቲዎስ በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት “አንድ እሽግ ለአንድ ተማሪ” በሚል መርሃ ግብር የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ በዳውሮ ዞን ከ2 ሺህ 400 በላይ ተማሪዎችን ማገዝ መቻሉን ገልጸዋል።

‎በዘንድሮ መርሃ ግብር ከ600 በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ ማገዝ መቻሉንም አብራርተዋል።

‎በመርሃ ግብሩ በርካታ ግለሰቦች፣ የመንግስት አካላት፣ ወጣቶችና የሥራ ኃላፊዎች በበጎነት ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚቻል ‎አቶ በሀይሉ ጠቅሰው፤ ፋውንዴሽኑ በቀጣይ ከትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ባሻገር በሌሎች ማህበረሰቡን በሚጠቅሙ መስኮች ላይ በመስራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱንም ገልጸዋል።

‎ወ/ሮ ዘርፍነሽ ብትሬ እና አቶ መኩሪያ ማቱሳላ በአቅም ማነስ ምክንያት ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ ለተደረገላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
በመርሃ-ግበሩ “አንድ እሽግ ለአንድ ተማሪ” የበጎነት መርሃ ግብር የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ያለባቸውን ተማሪዎች በመደገፍ፤ በትምህርት ተሳትፎና ውጤታማነት ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ የታለመ ተግባር መሆኑ ተገልጿል።

በዝግጅቱ የክልልና የዞን የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች፣ የታርጫ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ወላጆችና ተማሪዎች ተገኝተዋል።

”ኒው ዳውሮ ፋውንዴሽን” በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የሚንቀሳቀስ የበጎ አድራጎት ማህበር ነው፡፡

ዘጋቢ፡ ፋሲካ ሙሉጌታ – ከዋካ ቅርንጫፍ