ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ህዝብ ለህዝብ የሚያስተሳስርና አንድነታችንን ይበልጥ የምናጠናክርበት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ
ከ1 ሺህ 500 በላይ ኤሊት አትሌቶች የተሳተፉበት 6ኛው ዙር ኬሮድ ታላቅ የጎዳና ላይ ሩጫ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ህዝብ ለህዝብ የሚያስተሳስርና አንድነታችን የምናጠናክርበት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል።
የኬሮድ ሩጫ በክልሉ ተተኪ አትሌቶች የሚፈሩበት ውድድር እየሆነ መምጣቱን ያነሱት ሀላፊው ይህም ለሌሎች የስፖርት ማህበሮች ተምሳሌት መሆኑን ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደገለጹት፤ ስፖርት አንድነትን ከማጠናከር ባለፈ የሰው ልጅ ጤናው ተጠብቆ ረጅም ጊዜ መቆየት እንዲችል የሚያግዝ ነው።
መሰል የስፖርት አይነቶች ወጣቶች አልባሌ ስፍራዎች ላይ እንዳይውሉ የሚረዳ በመሆኑ በዞኑ የሚገኙ ተተኪ ስፖርተኞችን የሚያፈሩ ክለቦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ላጫ አመላክተዋል።
ኬሮድ ለዞኑ የአትሌቲክስ ዘርፍ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ የስፖርት ማህበር መሆኑን ያነሱት አቶ ላጫ በቀጣይም አለም አቀፍ ውድድር እንዲሆን ከማህበሩ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስረድተዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ የከተማውን ገጽታ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው በማስረዳት የማህብረሰቡን ባህላዊ እሴቶች ለሌሎች ለማሳየት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ሙራድ አክለውም ውድድሩ አብሮነትን ለማጠናከርና አካላዊ ብቃት ለመፈተሽ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመው ውድድሩ በከተማው መዘጋጀቱ ተተኪ አትሌቶች እንዲነሳሱበት እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ኬሮድ እንደ ስያሜው የአካባቢውን ሰላም ለማሳየት እንዲሁም የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ እና የአትሌቶችን ዝግጅት ለማበረታታት የሚዘጋጅ ውድድር መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኬሮድ ስፖርትና ልማት ማህበር ፕሬዝዳንት አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ናቸው።
በ6ኛው ዙር የኬሮድ የ15 ኪሎ.ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከ1 ሺህ 500 በላይ ኤሊት አትሌቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ከ30000 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ውድድሩን መታደማቸውን ገልጸዋል።
የኬሮድ የጎዳና ላይ ውድድር አትሌቶች ያደረጉትን ዝግጅት ለመገምገም የሚያግዝ መሆኑን ያነጋገርናቸው አትሌቶች ሲያነሱ ከባድ ፉክክር የነበረበት ፈታኝ ውድድር እነደነበር ጠቁመዋል።
በ6ኛው ዙር የኬሮድ የጎዳና ላይ ውድድር አትሌት አባይነህ አየለ በወንዶች ዘርፍ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆን አትሌት ማርታ ገ/ሚካኤል በሴቶች ዘርፍ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች።
ዘጋቢ፡ ዳዊት ዳበራ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ከ1500 በላይ ኤሊት አትሌቶች የሚሳተፉበት 6ኛው ዙር የኬሮድ የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በወልቂጤ ከተማ ተጀመረ
ቶትንሃም በአስቶንቫላ ተሸነፈ
አትሌት ልቅና አምባው ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ አስገኘች!