በትምህርቱ ዘርፍ ላይ መስራት የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ላይ መስራት እንደሆነ ተገለጸ
በትምህርቱ ዘርፍ ላይ መስራት የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ላይ መስራት እንደሆነ የሀዲያ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጸ/ቤት “ፍሬንድስ ኦፍ ሆመቾ” ከተሰኘ በጎ አድራጊ ድርጅት ጋር በመተባበር ለአንድ ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በድጋፍ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሃዲያ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዴታሞ ጡምደዶ እንደተናገሩት፤ በዞኑ የተለያዩ የበጎነት ስራዎች እየተሰሩ የቆዩ ቢሆንም በትምህርት ዘርፍ ላይ መስራት ግን የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ላይ መስራት በመሆኑ ከሌሎች ድጋፎች ይለያል ብለዋል።
የሁሉም ነገር መሰረትና ቁልፍ በሆነው ትምህርት ላይ መስራት ሁሉንም ዘርፍ መደገፍ መሆኑን የገለጹት አቶ ዴታሞ፤ ይህን በመረዳት ለአንድ ሺህ ህፃናት ድጋፍ ያደረገውን ፍሬንድስ ኦፍ ሆመቾ ድርጅት አመስግነዋል።
የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አድነው ባፋ በበኩላቸው፤ የብልጽግና መንግስት ሰው ተኮር የሆኑ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፤ እንደ ከተማ አስተዳደር በክረምት ወቅት ዘርፈ ብዙ የበጎ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
አቅመ ደካሞችን የመደገፍ ተግባር በመንግስት ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባው፤ ፍሬንድስ ኦፍ ሆመቾ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ያደረገው ድጋፍ የዚሁ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በትውልድ ላይ መስራት ለሃገር መስራት መሆኑን በመረዳት ድርጅቱ ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎችን በማገዙ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ አቦ በበኩላቸው፤ “በጎነት ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በከተማው በርካታ የበጎነት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ከእነዚህ መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በትምህርት ቁሳቁስ፣ በአልባሳት፣ በምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁሶች፣ መጠለያ ቤት የመስራትና የማደስ ድጋፎች ተጠቃሽ እንደሆኑ አንስተዋል።
ጽ/ቤቱ ከድርጅቱ ጋር በመተባበር ለአንድ ሺህ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም አቶ ተካልኝ ገልጸዋል።
ድጋፉን ያቀረቡት “የፍሬንድስ ኦፍ ሆመቾ” መስራችና አስተባባሪ አቶ አርጋው በዶሬ በድጋፉ ወቅት እንደገለጹት፤ ትምህርት የሁሉም ነገር ቁልፍ መሆኑን በመረዳት፤ ከልጅነት ዕድሜዬ ጀምሮ ዘርፉን ለመደገፍ የነበረኝን ራዕይ ወደ ተግባር የቀየርኩበት ስራ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ሁለት ቀናት በሀድያ ዞን በሆመቾ ከተማ አስተዳደር ለሁለት ሺህ ተማሪዎች ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቁመው፤ እየተደረጉ ያሉ የጤና፣ የውሃና የትምህርት ዘርፍ ድጋፎችን የበለጠ እንደሚያሳድጉም አሳውቀዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች እና ወላጆች በትምህርት ቁሳቁስ እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዳይሆኑ ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽንና የንግድ ትርዒት ተከፈተ
ኒው ዳውሮ ፋውንዴሽን ከ600 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አበረከተ
በኮሬ ዞን የሣርማሌ ወረዳ የፀጥታ ምክር ቤት ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ዙሪያ የጋራ ውይይት አደረገ