በበጀት አመቱ በክልሉ ከ160 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)

በበጀት አመቱ በክልሉ ከ160 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በበጀት አመቱ በክልሉ ከ160 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባኤ በወልቂጤ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ለጉባኤው ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ በሁሉም የምርት ወቅቶች 1 ሚሊዮን 259 ሺህ 472 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል።

የክልሉን አጠቃላይ የምርት መጠን በማጥናት የዕቅድ መነሻ ተደርጎ ወደ ተግባር ተገብቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለያዩ የሰብል አይነቶች 160 ሚሊየን 614 ሺህ 274 ኩንታል ምርት ማምረት መቻሉን አብራርተዋል።

በመኸር እርሻ በአዝዕርትና በሆርቲካልቸር ከ57 ሚሊየን 547 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው አብራርተዋል።

በክልሉ በበልግ የአዝመራ ወቅት 267 ሺ 817 ሄክታር ማሳ በማልማት ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ስለመገኘቱም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

በአዝዕርትና በሆርቲካልቸር ሰብሎች 437 ሺህ 182 ሄክታር ማሳ በማልማት ከ 62 ሚሊየን 872 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

በክልሉ በአትክልት፣ በቅባትና በስራስር ሰብሎች የላቀ ውጤት መመዝገቡን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

በምርት ዘመኑ በኩታ ገጠም እርሻ ከ6 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

በፀደይ ወቅት እርሻ 63 ሺ 540 ሄክታር መሬት በማልማት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው አንስተዋል።

በበጀት አመቱ በክልሉ በበጋ መስኖ ልማት ከ37 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ስለመገኘቱም አብራርተዋል።

በበጀት አመቱ የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ርዕሰ መስተዳደሩ በሪፖርታቸው ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ መለሰች ዘለቀ