በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማትና ሰላምን በማጽናት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተፈጥሮና የባህል ጸጋዎችን በአግባቡ በማልማት፣ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥና የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የአካባቢውን ማህበረሰብ በተለይም ወጣቶችን ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይንቱ መልኩ የተመራ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ፣ በደቡብ ኦሞ ዞን ሳላማጎ ወረዳ ሃና ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የታማ ማህበረሰብ የዱር እንስሳት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የሥራ ሂደት በአካል ተገኝቶ ተመልክቷል።
የሳላማጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ህጉ ቅጣቱ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ የቱሪዝም ልማት የአንድ ተቋም ብቻ የቤት ሥራ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ የሚጠይቅ አገራዊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
ወረዳው ለቱሪዝም መስክ እጅግ ምቹ የሆኑ በርካታ የባህልና የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት መሆኑን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፣ እነዚህን ጸጋዎች በአግባቡ በማልማት የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለክልሉና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና የመዳረሻና የቱሪዝም መሠረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተካልኝ ጌታሁን በበኩላቸው፤ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ማስፋፋትና ሀብቶችን ለአለም ማስተዋወቅ የቱሪዝም ዕድገት ዋና ዋና ምሰሶዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተቋሙ በአዋጅ አዲስ ሆኖ ከተደራጀ በኋላ በማዜ ፓርክ፣ በማጎ እና በሌሎችም አካባቢዎች ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን የመገንባት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፥ በግንባታ ላይ የሚገኘው የታማ ማህበረሰብ የዱር እንስሳት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት አሁን ላለበት ጥሩ ደረጃ እንዲደርስ የወረዳው አስተዳደርና የሚመለከታቸው አካላት ላደረጉት የላቀ አስተዋጽኦ በቢሮው ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ፕሮጀክቱ መንግስትና ብልጽግና ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ስትራቴጂ መሠረት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በአጠቃላይ አቅጣጫው ወደ 20 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ የጠየቀ መሆኑን ጠቁመዋል።
የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወይንቱ መልኩ በሰጡት ማጠቃለያ ንግግር፤ ቱሪዝም ወሰንና ቋንቋ የሌለው ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚና የባህል ድልድይ መሆኑን ገልጸው፣ ዘርፉን በስፋት ለማሳደግ ሰላም መሠረታዊ ቅድመ-ሁኔታ በመሆኑ ሰላምን በማጽናት ማህበረሰቡ ከዘርፉ በሚገኘው ገቢ ተጠቃሚ እንዲሆን ሁሉም አካላት በኃላፊነት ስሜት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አክለውም፣ ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶችና የዱር እንስሳት በጥንቃቄ በመጠበቅና በማልማት፣ በአካባቢው ያለውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም፣ የቱሪዝም ሀብቶቻችንን ለዓለም አቀፍ መድረክ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም ወጣቶች በቱሪዝም ዘርፍ በተለያዩ የሥራ እድሎች ተደራጅተው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።
የብርሃን ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሙሉቀን ታደሰ በበኩላቸው፤ የግንባታ ሥራውን ከተረከቡ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግንባታው ከ65 በመቶ በላይ መጠናቀቁንና በቀጣዮቹ 4 ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አጠናቀው ለማስረከብ በከፍተኛ ትጋት እየሠሩ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ሳውላ ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተካሄደ ነው
በተጠናቀቀው በጀት አመት እንደሃገር ሆነ በልዩ ወረዳው ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ስኬታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉ ተገለጸ
የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የስራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ