የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ በመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሰኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አሰታወቀ

የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ በመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሰኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አሰታወቀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 23/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት በመፍታት የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ በመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሰኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አሰታውቋል፡፡

‎በክልሉ መሰኖና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት ባለቤትነት በሣላማጎ ወረዳ እየተሰራ ያለውን ከሃና- ኦሞ ሮንቤ 10.04 ኪሎ ሜትር የመንገድ መሠረተ ልማት ተመልክቶ ወይይት አካሂዷል።

‎የወረዳው ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስልጣኑ ሉችኮሮ፤ የመንገድ ሥራው በዝናብና ሌሎች ምክንያቶች እንዳይስተጓጎል ከግንዛቤ ሥራዎች ጀምሮ የቅርብ ክትትል በማድረግ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመፍታት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

‎የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር አዳነ ሽብሩ፤ አንዳንድ የሚገጥሙ ችግሮችን የእርምት እርምጃ እየወሰደ የኘሮጀክቱ ሰራተኞች ከሥጋት ነፃ ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት ዋና ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ወደፊት ሥራብዙ እና የድርም ላንድ ኮንስትራክሽን ኘሮጀክት ማናጀር ይንገስ ታፈሬ በጋራ እንደገለፁት፤ ፕሮጀክቱ ከ75 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል የተገባ ነው።

‎ይሁን እንጂ በነዳጅ እና ሌሎች ምክንያቶች መስተጓጎሉን የገለፁት የሥራ ኃላፊዎቹ፤ አሁን ላይ ኘሮጀክቱ 8.8 ፊዚካል 7.04 ፋይናንሻል የተከናወኑ ሥራዎች ሲሆኑ መድረስ ከሚገባው 40 በመቶ በታች ቢሆንም ይህንን ለመሸፈን ለመንገድ ሥራው የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ከማምረት ጀምሮ ያሉ ሥራዎችን በፍጥነት በማከናወን በተባለው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

‎ኮንትራክተሩም ሆነ ሌሎችም በመንገድ ሥራው ላይ ያሉትን ውስንነቶች በማረም ኘሮጀክቱ በአካባቢው መገንባቱ ለወጣቱና ለተለያዩ የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ያለውን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እንደሚሰሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የተናገሩት የሣላማጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ህጉ ቅጣቱ እና የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የሠላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባናና ጠብልጉ ናቸው።

‎የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት የመሠረተ ልማት መሐንዲስ አቶ ዮሐንስ ገዛኸኝ፤ ወረዳው በአካባቢው መንገድ ሥራ ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮችን በቅንጅትና በውይይት በመፍታት ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አድንቀው አንዳንድ የአቅም ውስንነቶችን እየለዩ ለማረም እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

‎አክለውም የወረዳው መስተዳደር እና የዘርፉ አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍና ጥረት በማገዝ በቅንጅት ኮንትራክተሩ እና አማካሪ ድርጅቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡና በጊዜ በመወጣት አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚገባና እንደ ክልልም አሰፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል።

‎ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን