በቡና ልማት የተመዘገበውን ስኬት በማስቀጠል ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል ቀጣይ ትኩረት መሆኑ ተገለጸ

በቡና ልማት የተመዘገበውን ስኬት በማስቀጠል ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል ቀጣይ ትኩረት መሆኑ ተገለጸ

በጎፋ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽሕፈት ቤት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የቡና ምርትና ምርታማነት ማሻሻያ ኢኒሼቲቭ ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ፤ ቡና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰው የምርትና ምርታማነት ማሻሻያ ኢኒሼቲቮችን በተጠናከረ መልኩ በመተግበር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዞኑ በ2017/18 የምርት ዘመን ከ7 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው ይህም ቀደም ሲል በሄክታር 5 ኩንታል የነበረውን አማካይ ምርታማነት ወደ 7 ኩንታል ከፍ ለማድረግ አስችሏል ብለዋል።

አቶ ዳንኤል በተጨማሪም ሕገወጥ የቡና ዝውውር በግብይት ሥርዓቱና በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጠቁመው፤ ሕብረተሰቡ በቁጥጥርና በክትትል ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የጎፋ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑርአዲስ አደም በበኩላቸው፤ ቡናን በክላስተር በማልማትና የተለያዩ የግብርና ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችን በማስተባበር የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ጥራት ያለው ምርት ለማምረትና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ አካላትም የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም በማጎልበትና ሕገወጥ የቡና ዝውውርን በተጠናከረ ቁጥጥር ለመከላከል በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን