ሳውላ ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተካሄደ ነው
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን የሳውላ ከተማን ለነዋሪዎቿ ጽዱና ምቹ፣ ለባለሀብቶች ደግሞ ተመራጭ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ያለመ የ5 ኪሎ ሜትር የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
የሳውላ ከተማ አስተዳደር ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት የሚያካሂደው ይህ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፤ ከዛጎል የነዳጅ ማደያ እስከ ወንባ ወንዝ ድረስ የሚዘልቅ 5 ኪሎ ሜትር የመንገድ አካልን የሚሸፍን ነው።
የከተማው ከንቲባ አቶ በላይነህ ባህሩ እንደገለጹት፤ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ውብ፣ ንጹሕና ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባለፈ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በተቀናጀና በተሳሰረ መልኩ አሟልቶ የያዘ ነው ብለዋል።
በዚሁ መሠረት በግንባታው ሂደት ውስጥ ዘመናዊ የመንገድ መብራት አውታሮች፣ የውሃና የኤሌክትሪክ መስመሮች ዝርጋታ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የፍሳሽ ማስወገጃዎች፣ የመናፈሻ ሥፍራዎች፣ የሕዝብ መገልገያ ካፌዎች እንዲሁም የሕፃናት መጫወቻዎችና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች መካተታቸውን ከንቲባው አብራርተዋል።
ይህ አጠቃላይ ጥረት ከተማዋን ለመኖሪያነት ብቻ ሳይሆን ለመዝናኛ፣ ለንግድና ለሥራ ዕድል ፈጠራ እጅግ ምቹ በማድረግ በክልሉና በአገሪቱ አቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ መሠረት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ከተማዋ ያላትን ተፈጥሯዊ ጸጋዎች በመጠቀም የቱሪስት መዳረሻዎችንና የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ ይገኛል።
ከንቲባ አቶ በላይነህ አክለውም የኮሪደር ልማቱ የታቀደለትን ታላቅ ግብ ለማሳካት የሕብረተሰቡና የባለሀብቱ ንቁ ተሳትፎና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ ሳውላን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለቱሪስቶች ማራኪና ለባለሀብቶች ተመራጭ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀው፤ በገንዘባቸው፣ በማቴሪያልና በዕውቀታቸው ከከተማው አስተዳደር ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ: አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማትና ሰላምን በማጽናት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ምሁራን ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም ከአካባቢያቸው አልፈው ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
የዝናብ እጥረት የቡና ምርትን እንዳይጎዳ የማሳ እርጥበትን መጠበቅ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ