ሞሐመድ ሳላህ ወደ ቱርኩ ትራብዞን ስፖር የሚያደርገውን ዝውውር ለማጠናቀቅ ኢስታንቡል ገብቷል
የግብፅ እና የሊቨርፑል ታላቁ የፊት መስመር ተጫዋች ሞሐመድ ሳላህ የቱርክ ሱፐር ሊግ ክለብ የሆነውን ትራብዞን ስፖርን በነፃ ዝውውር ለመቀላቀል ኢስታንቡል አታቱርክ አየር መንገድ ገብቷል።
በቦታው የተገኙ በርካታ ደጋፊዎች ለግብፃዊው ኮከብ አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን ተጫዋቹ የትራብዞን ስፖርን ማሊያ ለብሶ በግል ጄት ላይ ሆኖ ለአድናቂዎቹ ሰላምታ ሲያስተላልፍ ታይቷል።
ሳላህ እስከ ሰኔ 2028 የሚያቆየውን የሁለት ዓመት ውል እንደሚፈርም ተረጋግጧል።
በዓመት አጠቃላይ እስከ 17.5 ሚሊዮን ዩሮ ደመወዝ እና የ5 ሚሊዮን የፊርማ አበል እንደሚያገኝም ተዘግቧል።
በሊቨርፑል እና በግብፅ ብሔራዊ ቡድን ይጠቀማቸው የነበሩትን 10 እና 11 ቁጥሮች ትቶ፣ ለትራብዞን ከተማ መለያ የሆነውን ቁጥር 61 ማሊያ እንደሚለብስ ተገልጿል።
በኢስታንቡል የሕክምና ምርመራውን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ትራብዞን ከተማ በማምራት በክለቡ ደጋፊዎች ፊት በይፋ ተዋውቆ የፊርማ ስነ-ስርዓቱን ያከናውናል ተብሎ ይጠበቃል።
በሊቨርፑል ቤት በነበረው 9 ዓመታት 257 ግቦችን በማስቆጠር የክለቡ ታሪካዊ ተጫዋች መሆን የቻለው ሳላህ፤ ውሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ነፃ ተጫዋች ሆኖ ይገኝ ነበር።
ቀደም ሲል ከሌላው የኢስታንቡል ክለብ ቤሺክታሽ ጋር ንግግር አድርጎ የነበረ ቢሆንም በክፍያ እና በምስል መብት ባለመስማማታቸው ዝውውሩ ፈርሷል።
ይህን ተከተሎ ትራብዞን ስፖር በፍጥነት ዝውውሩን በማንቀሳቀስ የቱርክ እግር ኳስ ታሪክ ትልቁ ከሚባሉት ዝውውሮች አንዱን ማጠናቀቅ ችሏል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ሪያል ማድሪድ ያን ዲዮማንዴን በታሪካዊ የዝውውር ክፍያ አስፈረመ
ብሩኖ ጊማሬስ የሕክምና ምርመራውን በስኬት አጠናቀቀ
9 ክለቦች በአዲስ አሰልጣኞች ፍልሚያቸውን የሚጀምሩበት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ