ቪኒሲየስ ጁኒየር ከሪያል ማድሪድ ጋር የሚያደርገውን ድርድር በዚህ ሳምንት ዳግም እንደሚጀምር ተገለጸ
የላሊጋው ግዙፍ ክለብ ሪያል ማድሪድ ከክንፍ አጥቂው ቪኒሲየስ ጁኒየር ጋር የሚያደርገውን የኮንትራት ማደስ ድርድር በዚህ ሳምንት ዳግም እንደሚጀምር ተገልጿል።
ሎስብላንኮዎቹ ስምምነት ላይ ካልደረሱ ተጫዋቹን ለማስፈረም የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑ አርሰናል ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተለ ይገኛል።
የ 26 ዓመቱ ቪኒሺዬስ ጁኒዬር ከሪያል ማድሪድ ጋር አሁን ያለው ውል በሚቀጥለው ዓመት የሚያበቃ በመሆኑ ክለቡ ተጫዋቹን በነፃ እንዳያጣ ስጋት ውስጥ ገብቷል።
ላለፉት 18 ወራት ሲካሄድ የቆየው ውይይት የዘገየው በክለቡ በደመወዝ መጠን እና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ጉዳይ ከስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው ምክንያት መዘግየቶች አጋጥመውታል።
ኪሊያን ምባፔ ወደ ክለቡ ከመምጣቱ በፊት የቡድኑ ዋነኛ መሪ ሆኖ የቆየው ቪኒሲየስ፤ በፋይናንስ በኩል የክለቡ ከፍተኛ ተከፋይ ሆኖ የመታወቅ ፍላጎት አለው።
ቪኒሲየስ በክለቡ ከፍተኛ ተከፋይ ከሆኑት መካከል አንዱ ለመሆን የሚፈልግ ቢሆንም፤ ሪያል ማድሪድ የደመወዝ ስኬሉን ለመጠበቅ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ የክለቡን የደሞዝ መዋቅር ለመጠበቅ ጥብቅ አቋም ያላቸው ቢሆንም፤ ክለቡ በዚህ ሳምንት ውይይቱን በበጎ መንገድ ለማጠናቀቅ ተስፋ አድርጓል።
ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጋር ከነበረው የዓለም ዋንጫ ቆይታ በኋላ ዕረፍት ላይ ሰንብቶ በትናንትናው ዕለት ወደ ማድሪድ ተመልሶ የቅድመ-ውድድር ዘመን ዝግጅት የጀመረው ቪኒሲየስ፤ የአዲሱን አሰልጣኝ ሆሴ ሞውሪንሆን ስብስብ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀላቅሏል።
አሰልጣኝ ሆሴ ሞውሪንሆ ብራዚላዊው አጥቂ በክለቡ እንዲቆይ እና የወደፊት እጣ ፈንታውን ወደ ማድሪድ እንዲያዘንብል እንደሚፈልጉ ታውቋል።
የሪያል ማድሪድ እና የቪኒሲየስ ድርድር ውጤት ካላገኘ፣ የመድፈኞቹ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ተጫዋቹን ወደ ሰሜን ሎንዶን ለማምጣት ዝግጁ ናቸው።
ባለፈው የውድድር ዘመን የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሱት መድፈኞቹ፣ ቡድናቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ቪኒሲየስን ዋነኛ የግራ ክንፍ ግባቸው አድርገውታል።
ተጫዋቹ አሁንም ቢሆን በሪያል ማድሪድ ኮንትራት የማደሱን ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነ ተገልጿል።
አርሰናሎችም ቢሆኑ የተጫዋቹ ኮንትራት መጠናቀቂያ ላይ ቢደርስም ዝውውሩን ለማካሄድ የመጨረሻው ውሳኔ በተጫዋቹ እጅ ላይ መሆኑን ተረድተዋል።
ሪያል ማድሪድ እና ቪኒሲየስ በዚህ ሳምንት በሚያደርጉት ድርድር ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ፣ አርሰናል ለተጫዋቹ ጥያቄ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑ ተዘግቧል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገው ድርድር ውጤት የቪኒሲየስን የወደፊት እጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆን የዘመኑን ትልቁን የዝውውር እንቅስቃሴ የሚወስን ይሆናል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
ቪኒሲየስ ጁኒየር ከሪያል ማድሪድ ጋር የሚያደርገውን ድርድር በዚህ ሳምንት ዳግም እንደሚጀምር ተገለጸ

More Stories
“አርሰናል በዝውውር መስኮቱ ትልልቅ እቅዶች አሉት” – ሚኬል አርቴታ
አርሰናል የብሩኖ ጊማራኤስን ዝውውር ለማጠናቀቅ ከስምምነት ደረሰ!
ማንችስተር ዩናይትድ ሉዊስ-ስኬሊን ለማስፈረም እንቅስቃሴ ጀምሯል