በመንግስት መሥሪያ ቤቶች የንብረት ግዢ፣ ጥራትና አያያዝ ችግር በህዝብና በመንግስት ሀብት ላይ የሚያስከትለውን ብክነት ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን የባስኬቶ ዞን ፋይናንስና ፕላን መምሪያ አስታወቀ
መምሪያው በዞኑ ለረጅም ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ከ 15 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመንግስት ንብረቶችን በህጋዊ መንገድ በጨረታ በመሸጥ አስወግዶ ወደ ሀብት ለመቀየር ሂደት መጀመሩም አመላክቷል።
በባስኬቶ ዞን ከአመታት በፊት ተገዝተው በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት ያቆሙ በጨረታ የሚወገዱ የ15 ሚሊዮ ብር በላይ ግምት ያላቸው ተንቀሳቃሽና ቋሚ ንብረቶች እንደሚገኙ ተገልጿል።
ንብረቶች ለረዥም ጊዜያት አገልግሎት ሳይሰጡ ከመቆዬታቸው ባሻገር የተቀመጡበት አግባብ እንዲጎዱ ሲያደርጋቸው ቆይቷል።
በቅርቡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት በያዘው አቋም መነሻ ከዞኑ አስተዳደር እና ከፋይናንስ መምሪያ ጋር በመቀናጀት ያረጁና አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች በህጋዊ መንገድ ለሺያጭ ቀርበው እንዲወገዱ በማድረግ ወደ ሀብት የመቀየር ሥራ መጀመሩን የባስኬቶ ዞን ፋይናንስና ፕላን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉ መንገሻ ተናግረዋል።
ሂደቱ ጤናማና ግልጽ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ውሳኔ እንዲሰጡበትና አብሮ በመሥራት መርህን የተከተለ መሆኑንም አብራርተዋል።
በፋይናንስ መምሪያው በነበረው የጨረታ ሂደት ላይ ከተሳተፉ ተጫራቾች አንዳዶቹ በሰጡት አስተያየት፤ የንብረቶቹ መወገድ የአካባቢ ብክለትን ከመቀነስ ባሻገር ለሌሎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ያነሳሉ።
የመንግስት መሥሪያ ቤቶች የንብረት ግዢ ጥራትና አያያዝ ችግር የመገልገያ ቁሳቁሶች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ሳይሰጡ ያለ ጊዜ ለብልሽት እንዲጋለጡ በማድረግ የህዝብና የመንግስት ሀብት ያለአግባብ እንዲባክን መነሻ እየሆነ መቆየቱም ተገልጿል።
በግዢ ሂደት ላይ የተቀመጡ መመሪያዎችን በመተግበር የተለያዩ የቁጥጥር መለኪያዎችን አዘጋጅቶ መሥራት እንደ መፍትሄ መቀመጡም ተመላክቷል።
ከፍተኛ ሀብት ፈሶባቸው የሚገዙ ንብረቶች ያለ ጊዜያቸው እንዳይበላሹና ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ በየጊዜው የንብረት ቆጠራ እንደሚከናወንም ተብራርቷል።
ተቋሙ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የትኛውም የመንግስት ንብረት ተጠቃሚ የሆኑ አካላት ንብረቱን በተገቢው መንገድ በመጠቀም የሞራል ግዴታቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።
ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
በቡና ልማት የተመዘገበውን ስኬት በማስቀጠል ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል ቀጣይ ትኩረት መሆኑ ተገለጸ
የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የከምባታ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ
በጎፋ ዞን በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ8 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ