“አርሰናል በዝውውር መስኮቱ ትልልቅ እቅዶች አሉት” – ሚኬል አርቴታ

“አርሰናል በዝውውር መስኮቱ ትልልቅ እቅዶች አሉት” – ሚኬል አርቴታ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ አርሰናል በዘንድሮው የክረምት የዝውውር መስኮት ዝም ብሎ እንደማይቀመጥ እና በጣም ግዙፍ እቅዶች እንዳሉት ዋና አሰልጣኙ ሚኬል አርቴታ አስታውቀዋል።

መድፈኞቹ የቅድመ ውድድር ጨዋታቸውን ቅዳሜ ዕለት ዢሮናን 4 ለ 1 በማሸነፍ የጀመሩ ሲሆን፤ አዲሱ ፈራሚ ክርስቶስ ዞሊስ በመጀመሪያ ጨዋታው የመጀመሪያ ግቡን ማስቆጠር ችሏል።

ግሪካዊው ኢንተርናሽናል ኮከብ ብሩጅ በ40 ሚሊዮን ዩሮ ወደ ኤሚሬትስ የመጣ ሲሆን፣ በክረምቱ አርሰናልን የተቀላቀለ የመጀመሪያው የሜዳ ላይ (outfield) ተጫዋች ሆኗል።

አርሰናል ከዚህ ቀደም የፒዬሮ ሂንካፒዬን የውሰት ውል ወደ ቋሚነት የለወጠ ሲሆን፤ የቀድሞውን የሊድስ ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ኢላን መሲሊየርን በነጻ ዝውውር ማሰረሙ ይታወሳል።

ሆኖም አርሰናል አሁንም በዝውውር ገበያው በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል።

ክለቡ የሪያል ማድሪዱን ቪኒሲየስ ጁኒየር ዋና ኢላማው አድርጓል ከኒውካስል ዩናይትድ ለመውጣት ፍላጎት ያሳየውን እና አርሰናልን መቀላቀል የሚፈልገውን ብሩኖ ጊማራኤሽን ለማስፈረም ከስምምነት ላይ ደርሷል።

በተጨማሪም በጉዳት ላይ የሚገኘውን ዊሊያም ሳሊባን ቦታ የሚሸፍን የመሀል ተከላካይ ለማስፈረም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቡድኑን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተጨማሪ የግል ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።

በዝውውር መስኮቱ ተጨማሪ እርምጃዎች ይጠበቃሉ ወይ ተብለው ሲጠየቁ”ቡድናችንን ለማሻሻል እና ለማሳደግ በከፍተኛ ንቅናቄ ላይ እንገኛለን። በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ እንቅስቃሴዎች እንደሚኖሩ እንጠብቃለን” ብለዋል።

አርቴታ ምክንያቱን ሲያስረዱ”ምክንያቱም እንደማንኛውም ክለብ እኛም የበለጠ ጥንካሬ ማግኘት እንፈልጋለን። ተፎካካሪዎቻችን በዝውውር ገበያው ምን እያደረጉ እንደሆነ ማየት ይቻላል። እኛ ዝም ብለን አንቀመጥም፤ ለመድረስ የምንፈልግበት ቦታ በጣም ትልቅ በመሆኑ ከፍተኛ ምኞት አለን” ሲሉ ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሱትና በቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ በፓሪስ ሴንት ዠርሜን በመለያ ምት ተሸንፈው ሁለተኛ የወጡት መድፈኞቹ፤ አሁንም ቡድናቸውን ማጠናከር ለምን እንደፈለጉ አርቴታ ሲያስረዱ”ምክንያቱም በውድድሮች መካከል ያለው ልዩነት በጣም አነስተኛ ስለሆነ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

አሰልጣኙ እንዳሉት “የውድድሩ ደረጃ በሚጨምርበት ጊዜ የበለጠ ለመሻሻል ከፈለግን በቡድናችን ውስጥ ያለውን የቡድን ጥልቀት ደረጃ ማሳደግ አለብን። የላቀ ልዩነት ለመፍጠር በቡድናችን ውስጥ የጎደሉንን ነገሮች ለይተን ማሟላት ይኖርብናል። የማሰብያ መንገዳችን እሱ ነው” ብለዋል።

አርሰናል የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫውን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን አዲስ የውድድር ዘመን የፊታችን ነሐሴ 15 ኮቨንትሪ ሲቲን በኤሚሬትስ ስታዲየም በማስተናገድ ይጀምራል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ