በቀቤና ልዩ ወረዳ ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የልዩ ወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ

በቀቤና ልዩ ወረዳ ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የልዩ ወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ

ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም በልዩ ወረዳው በፈረጀቴ ቀበሌ ክልል አቀፍ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እወጃ የክልሉና የልዩ ወረዳው ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ነዋሪዎች በተገኙበት ከማለዳ 12፡00 ጀምሮ እንደሚከናወንም ተጠቁሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያዊያን በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ሌላ ታሪክ ለመስራት እንዘጋጅ በማለት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብድልሽኩር ደሊል እንደገለፁት በልዩ ወረዳው ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ አቅርቦት፣ የጉድጎድ፣ የመሳሪያ፣ የትራንስፖርትና ሌሎችም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል።

በልዩ ወረዳው በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 350 ሺህ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ የገለፁት አቶ አብድልሽኩር በተለይም ክልል አቀፍ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እወጃ በልዩ ወረዳው በፈረጀቴ ቀበሌ ከፍተኛ የክልሉና የልዩ ወረዳው አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ነዋሪዎች በተገኙበት ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም መላው የልዩ ወረዳው ማህበረሰብ በነቂስ በመውጣትና በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብሩ ላይ በመሳተፍ ታሪክ መስራት እንዳለበት ሃላፊው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን