ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ሐምሌ 27 የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሀ-ግብርን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ሐምሌ 27 የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሀ-ግብርን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

ሐምሌ 27 የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ በኅብረት ተስፋን በመትከል ሌላ ታሪክ ልናስመዘግብ ይገባል!

በክልላችን ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም በሚካሄደው የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ 69 ሚሊዮን ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በኅብረት በመትከል፤ እንደ ሀገር ለተያዘው 800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ግብ ስኬት አስተዋጽኦ የተስፋ አሻራችንን በማኖር ዳግም ሌላ ታሪክ ልናስመዘግብ ይገባል፡፡

አረንጓዴ አሻራ ለህልውናችን መሠረት የሆነን ብዝኃ ህይወት ከመጥፋት ለመታደግ፤ እንደ ውሀና አፈር ያሉ መተኪያ የሌላቸው የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በመጠበቅ የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመግራት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ ዘላቂ ልማትና ሁለንተናዊ ብልጽግና መሠረት የሚጥል መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡

ለናዳና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ የሆነ ሥነ-ምኅዳር በሚበዛው ክልላችን፤ በጋራ አረንጓዴ አሻራችንን ማኖራችን የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትን በዘለቄታዊነት ከመግታት ባሻገር ተራሮቻችንን ከስጋት ምንጭነት ወደ ሀብት ምንጭነት ማሻገር የሚያስችል በመሆኑ፤ በዘንድሮ የአንድ ጀንበር ተከላችንም በንቃት በመሳተፍ የተፈጥሮ ሚዛኑ የተጠበቀ አረንጓዴ ከባቢን ለትውልድ ለማዉረስ የጀመርነውን ጥረት እንድናጠናክር አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡

መላው የክልላችን ሕዝቦች፤ በነገው የአንድ ጀንበር ተከላ በየአካባቢው በተዘጋጁ የተከላ ቦታዎች በመገኘት፤ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምረን ቢያንስ ከ15 በላይ ችግኞችን በመትከል በከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት በተከላ መርሃ ግብራችን በንቃት በመሳተፍ እንደተለመደው በኅብረት ታሪክ እንድንሰራ ከአደራ ጭምር ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

በጋራ ተስፋ እንተክላለን!

የአካባቢያችንን ደህንነት በአረንጓዴ አሻራችን እናረጋግጣለን!!

ጥላሁን ከበደ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር