ማንችስተር ዩናይትድ ሉዊስ-ስኬሊን ለማስፈረም እንቅስቃሴ ጀምሯል

ማንችስተር ዩናይትድ ሉዊስ-ስኬሊን ለማስፈረም እንቅስቃሴ ጀምሯል

ማንችስተር ዩናይትድ የአርሰናሉን ሁለገብ ተከላካይ ማይልስ ሉዊስ-ስኬሊን ለማስፈረም የሚቻልበትን ሁኔታ እያጠና ይገኛል።

ዩናይትድ በሌላ በኩል የኒውካስል ዩናይትዱን ተከላካይ ሉዊስ ሆልን በእጁ ለማስገባት ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

የማንችስተር ዩናይትድ ከፍተኛ አመራሮች ለረጅም ጊዜ ለሉዊስ-ስኬሊ የነበራቸውን ፍላጎት መነሻ በማድረግ፣ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ትልቅ ወጪ ለማውጣት ባቀዱት መርሃ-ግብር መሰረት አርሰናል ተጫዋቹን ለመሸጥ ፍቃደኛ ይሆን እንደሆነ ለመፈተሽ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

በያዘነው የዝውውር መስኮት የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ትላልቅ ዝውውሮችን ለማከናወን በዝግጅት ላይ በመሆኑ፣ የዩናይትድ አመራሮች የዝውውር በር ሊከፈትልን ይችላል በሚል ተስፋ ሁኔታዎችን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

ባለፈው የውድድር ዘመን ሉዊስ-ስኬሊ ለረጅም ጊዜ ከቋሚ አሰላለፍ ውጪ ሆኖ ቢቆይም፣ በውድድር ዘመኑ ማጠቃለያ ላይ ያሳየው አስደናቂ ብቃት የክለቡን እይታ ቀይሮታል።

ወጣቱ ተጫዋች አርሰናል ከፓሪስ ሴንት ዠርሜን ጋር ባደረገው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ በቋሚነት ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን፣ ክለቡ ዋንጫውን ለማንሳት ባደረገው የመጨረሻ ትግል ላይ ወሳኝ ጉልበትና አስተዋፅኦ አበርክቷል።

አርሰናሎች ተጫዋቹን አሁንም በክለባቸው ማቆየት ቢመርጡም፣ የታሰቡት ትላልቅ ዝውውሮች ከተሳኩ ግን የሉዊስ-ስኬሊ ሁኔታ ሊቀየር እንደሚችል ይታመናል።

አርሰናል የኒውካስል ዩናይትዱን አማካኝ ብሩኖ ጊማራኤስን እና የሪያል ማድሪዱን ኮከብ ቪኒሲየስ ጁኒየርን የማስፈረም ትልቅ ዝውውር ከፈፀመ የቡድኑ ስብስብ አወቃቀር ሙሉ በሙሉ ሊለወጥ ይችላል።

ይህ አዲስ ስልታዊ ለውጥ ደግሞ ሉዊስ-ስኬሊ በቡድኑ ውስጥ ያለውን ቦታ እንደገና እንዲገመግም ሊያስገድደው እንደሚችል ተገምቷል።

እንዲሁም አርሰናል እነዚህን ውድ ዝውውሮች ከፈፀመ የፋይናንስ ሚዛኑን ለመጠበቅ ተጫዋቾችን መሸጥ ይኖርበታል።

ሉዊስ-ስኬሊ አርሰናል በዋናነት ለመሸጥ ከያዛቸው ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ባይኖርም፣ ለሌሎች ጥያቄዎች ግን በሩ ክፍት ነው።

በሌላ በኩል ማንችስተር ዩናይትድ የኒውካስል ዩናይትዱን የግራ መስመር ተከላካይ ሉዊስ ሆልን ለማስፈረም ትልቅ ተስፋ አድሮበታል።

በኒውካስል ዩናይትድ ባለቤቶች አዲስ ቡድን ለመገንባት በሚደረገው ስትራቴጂ ምክንያት ክለቡ የለውጥ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን፣ ሉዊስ ሆል ወደ ዩናይትድ ለመዛወር ፍላጎት እንዳለው ተገልጿል።

ምንም እንኳን የሁለቱ ተጫዋቾች ዝውውር እውን ለመሆን በርካታ ውስብስብ ድርድርና ትልቅ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የማንችስተር ዩናይትድ አመራሮች የክረምቱን የዝውውር መስኮት በበላይነት ለማጠናቀቅ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ተነግሯል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ