የቪኒሲየስ ጁኒየር እና ሪያል ማድሪድ ውጥረት፡ “ተቀበል ወይም ልቀቅ!”

የቪኒሲየስ ጁኒየር እና ሪያል ማድሪድ ውጥረት፡ “ተቀበል ወይም ልቀቅ!”

በሪያል ማድሪድ እና በብራዚላዊው ኮከብ ቪኒሲየስ ጁኒየር መካከል ለወራት ሲያያንዣብብ የነበረው የውል ማደስ አለመግባባት አሁን ወደ ከረረ ደረጃ ተሸጋግሯል።

የክለቡ የበላይ አካላት ለተጫዋቹ ወኪሎች የመጨረሻውን የውል ማደሻ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን “በቀረበው ውል መሠረት ትፈርማለህ፤ ካልሆነ ግን በዚህ ክረምት የዝውውር መስኮት እንሸጥሃለን” የሚል ግልጽ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።

በቫልደቤባስ (የክለቡ ማሠልጠኛ ማዕከል) ያለው የክለቡ አመራር አሁን ባለው እርግጠኝነት የጎደለው ሁኔታ መቀጠል እንደሌለበት ወስኗል።

በተለይም የእንግሊዙ አርሰናል ተጫዋቹን ለማስፈረም ያሳየው ፍላጎት፣ ሪያል ማድሪድ የቪኒሲየስን የወደፊት እጣ ፈንታ በፍጥነት ለመቋጨት መወሰኑን ማርካ ዘግቧል።

እንደ ማርካ ዘገባ ከሆነ ክለቡ ያቀረበው ጥያቄ የመጨረሻው ነው። ከዚያ በላይ የደመወዝ ጭማሪ ወይም ተጨማሪ የድርድር መድረክ አይኖርም።

ቪኒሲየስ የቀረበለትን ጥያቄ ካልተቀበለ፤ ማድሪድ ኮንትራቱ አልቆ በነፃ ከሚወጣ ይልቅ በዚህ በአሁኑ የዝውውር ወቅት ለሽያጭ ያቀርበዋል።

ሪያል ማድሪድ ለቪኒሲየስ ላበረከተው አስተዋጽኦ ተገቢውን የገንዘብ ክፍያ መክፈል ቢፈልግም፤ የቡድኑን የደመወዝ መዋቅር ግን ለአንድ ተጫዋች ሲል እንደማያፈርስ አረጋግጧል።

ተጫዋቹ ውሉን ሳያድስ በክለቡ ለመቆየት ቢመርጥ እንኳ በሁለቱም የክንፍ መስመሮች ላይ መጫወት የሚችለው ያን ዲዮማንዴ ወደ ክለቡ ሊቀላቀል መቃረቡ ለአሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ጠንካራ አማራጭ የሚፈጥርላቸው ይሆናል።

ይህም ማድሪድ በቪኒሲየስ ላይ ያለውን ጥገኝነት የሚቀንሰው በመሆኑ፡ የውል አለመግባባቱ ካልተፈታ ብራዚላዊው ኮከብ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ለመቀመጥ እንደሚገደድ ይገመታል።

ሪያል ማድሪድ ለቪኒሲየስ ያስቀመጠው አማራጭ ግልጽ እና ጥብቅ ነው – “ቀጣይነቱን ማረጋገጥ ወይም ደብተር ዘግቶ መስናበት!”

ኳሷ አሁን በቪኒሲየስ እግር ስር ትገኛለች።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ