በክረምቱ ወቅት የሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ከማስቻሉም በላይ ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ዝግጅት ከፍተኛ እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ ትምህርት እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች ገለፁ

በክረምቱ ወቅት የሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ከማስቻሉም በላይ ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ዝግጅት ከፍተኛ እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ ትምህርት እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች ገለፁ

በትምህርት ዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ለማስቻል በከተማው በበጎ ፈቃደኞች የሚሰጠው የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በክረምት በጎ ወጣቶች በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ የሆሳዕና ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

”በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በመላው ሀገሪቱ የሚከናወኑ ማህበረሰብ አቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በክረምቱም ተጠናክረው ቀጥለዋል።

በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የዘንድሮው የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ15 በላይ ዘርፎች እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን፣ በእረፍት ላይ በሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን የሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት ከእነዚህ መካከል ተጠቃሽ ነው።

በከተማው በኃይሌ ቡባሞ አንደኛና መካከለኛ ትምህርት ቤት ተገኝተን ያነጋገርናቸው ተማሪዎች፤ የክረምቱን እረፍት ከትምህርት ጋር በማጣመር ለመጪው ዓመት የሚያግዛቸውን ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ትምህርቱ በዋናነት በሳይንስ፣ በሂሳብ እና በቋንቋ የትምህርት ዓይነቶች ላይ ያተኮረ መሆኑን የገለጹት ተማሪዎቹ፤ ይህም በመደበኛው የትምህርት ወቅት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እንደሚያስችላቸው ገልፀዋል።

በመሆኑም ሌሎች ተማሪዎችም ጊዜያቸውን በከንቱ ከማባከን ይልቅ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉ የትምህርት እድሎችን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል በበጎ ፈቃደኝነት ትምህርቱን እየሰጡ የሚገኙ መምህራንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ ሀገር የምትገነባው በተማረና በሚያገናዝብ ትውልድ በመሆኑ ያለ ምንም ቀስቃሽ የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

አክለውም በተማሪዎች ዘንድ ውስብስብ ሊሆኑ የሚችሉ አርዕስቶችን በመለየትና በዕቅድ በመመራት የማጠናከሪያ ትምህርቱን እየሰጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኪበሞ ሰለሞን በበኩላቸው፤ በከተማው ከ15 በላይ በሚሆኑ ማህበራዊ ዘርፎች የበጎ ፈቃድ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልፀው የትምህርት ዘርፉ ዋነኛው መሆኑን ጠቁመዋል።

የጎልማሶችን ትምህርት በማካተት በከተማው ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን የተናገሩት ኃላፊው፤ይህም በመደበኛው የትምህርት ዘመን በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን