ውድና ውስን የሆነውን መሬት ያለብክነት ለመምራትና ለመጠቀም እየተሰራ ነው – የባስኬቶ ዞን አስተዳደር

ውድና ውስን የሆነውን መሬት ያለብክነት ለመምራትና ለመጠቀም እየተሰራ ነው – የባስኬቶ ዞን አስተዳደር

ውድና ውስን የተፈጥሮ ሀብት የሆነውን መሬት ያለብክነት ለመምራትና ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን የባስኬቶ ዞን መሬት አስተዳደር መምሪያ አስታወቀ።

‎‎መምሪያው የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2019 ዕቅድ ማስፈፀሚያ ንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

‎የባስከቶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር በዛብህ ገበየሁ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ መሬት የማይተካ ውድ የተፈጥሮ ሀብት በመሆኑ መንግስት ይህንን ሀብት በህግ፣ በግልፀኝነት፣ በፍትሀዊነትና በተጠያቂነት ለማስተዳደር የመሬት አስተዳደር ህግና መመሪያ አውጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

‎የመሬት መረጃ ሥርዓቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማጠናከር የባለይዞታዎችን መረጃ ከብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት ጋር በማስተሳሰር የመሬት ምዝገባን ቀልጣፋ፣ ግልጽና አስተማማኝ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

‎የመሬት ሀብትን ከብክነትና ከሙስና በመጠበቅ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል።

‎ህገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግብይትን መከላከል፣ ሕገ-ወጥ ይዞታዎችን በሕግ ማዕቀፍ መፍታት፣ የመሬት ምዝገባና መረጃ ሥርዓትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማዘመን እና የገጠር ይዞታ ሰርተፊኬትን ለፋይናንስ ተደራሽነት ለመጠቀም እንደሚሰራም ተናግረዋል።

‎የዞኑ የመሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤፍረም ስዩም በበኩላቸው፤ ውድና ውስን የሆነውን የተፈጥሮ ሀብት ያለብክነት በመምራትና በመጠቀም ወደ ሀብትነት መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል።

‎ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን የመሬት ወረራ እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቆጣጠር እንደሚገባም ተናግረዋል።

‎የአርሶአደሩን የይዞታ መብት በማረጋገጥ ዜጎች ያለስጋት በይዞታቸው ላይ አልምተው እንዲጠቀሙ በትኩረት በመስራት ዘመናዊ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

‎በመድረኩ የመምሪያው የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2019 ዕቅድ፣ የመሬት አስተዳደር ደንብ፣ ሳይፈቀዱ የተያዙ ይዞታዎች ህጋዊ ስርዓት የማስያዝ ስርዓትና የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓት ዙሪያ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎበታል።

‎የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት መሬት ከዚህ ቀደም ልቅ በሆነ ሁኔታ ከሚተዳደርበት መንገድ በማላቀቅ የራሱ ባለቤት የሆነ ተቋም መፈጠሩና በህግ እንዲተዳደር መደረጉ ከመሬት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ እንደሚረዳ ገልፀዋል።

‎ዘጋቢ፡ አብርሃም ኩምሳ – ከሣውላ ጣቢያችን