በጎፋ ዞን ጋልማ ከተማ በ2019 በጀት ዓመት ከ18 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱ ተገለፀ
በከተማው በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ ስራ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የጋልማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ቡካሮ ደቦጭ በ2018 በጀት ዓመት ከ1 ሺህ 400 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
ወጣቶቹ በኢንዱስትሪ፣ ከተማ ግብርና እና በአገልግሎት ዘርፎች መሠማራታቸውን እና 96 በመቶ የሚሆኑት ቋሚ የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ጠቁመዋል።
በ2019 በጀት ዓመትም ከ18 ሺህ በላይ የሚሆኑ ስራ አጥ ወጣቶችን በመለየት የስራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀው፤ ለዚህም አስፈላጊ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አመላክተዋል።
ለወጣቶቹ የመስሪያና መሸጫ ቦታ ከማመቻቸት ጀምሮ የማምረቻ ግብዓት አቅርቦትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ትኩረት እንደተሰጠው አቶ ቡካሮ ጠቁመው፤ ከ1 ሚሊየን 782 ሺህ ብር በላይ ለብድር ስርጭት መያዙንም አስታውቀዋል።
በጋልማ ከተማ በማህበር ከተደራጁ ወጣቶች መካከል ያነጋገርናቸው የአማዶ ዛላ እንጨትና ብረታብረት ስራ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ሙሉጌታ ሙሴ እንደተናገረው፤ ማህበሩ በአሁን ሰዓት የኢኮኖሚ አቅሙን እያጎለበተ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሶ፤ 10 ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስረድቷል።
የጋልማ ፉልቶ ወተት ማህበር ሰብሳቢ በበኩላቸው፤ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም የወተት ምርታቸውን ከፍ በማድረግ በቀን እስከ 60 ሊትር ወተት እያገኙ የገቢ አቅማቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ እንዳሻሻሉ ተናግረዋል።
ለስኬታማነታቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የማህበሩ አባላት የሚመሰክሩት መሆኑን ገልጸዋል።
የጋልማ ብሎኬት ማምረቻ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት እሰየ እሸቱ ተደራጅተው በጀመሩት ስራ ካፒታላቸውን ከ800 ሺህ ብር በላይ ማስመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ: ድጋፌ ድክሬ – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
ውድና ውስን የሆነውን መሬት ያለብክነት ለመምራትና ለመጠቀም እየተሰራ ነው – የባስኬቶ ዞን አስተዳደር
የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓልን ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
ጦርነቱ ሳዉዲ አረቢያ እና ሁቲ በከፈቱት የተኩስ ልውውጥ እንደ አዲስ አገርሽቷል