“እናቴ ሆይ ደውይልኝ!”
በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎችና በብራዚል ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የምናየው አጥቂ ጋብርኤል ጄሱስ ጎል ባስቆጠረ ቁጥር በጣቶቹ የስልክ ምልክት በመስራት ደስታውን ሲገልጽ ይታያል።
ብዙዎችን የሚያስደምመውና “አሎ እናቴ” (Alô Mãe) በሚል ስም የሚታወቀው ይህ ልዩ የደስታ አገላለጽ ከጀርባው ልብ የሚነካ እና አስገራሚ ታሪክ አዝሏል።
ጋብርኤል ጄሱስ ያደገው በብራዚል ሳኦ ፓውሎ ከተማ ድሃ ሰፈር ውስጥ ሲሆን፣ አባቱ ገና በሕፃንነቱ ስለሞቱ እናቱ ቬራ ሉቺያ ዳ ሲልቫ ብቻዋን ሶስት ወንዶችና አንዲት ሴት ልጅ በትግል አሳድጋዋለች። እናቱ በሕይወቱና በእግር ኳስ እስካሁን ላስመዘገበው ስኬት ትልቁን ድርሻ ትወስዳለች።
ጄሱስ እንደሚናገረው ከሆነ ከእያንዳንዱ ጨዋታ በፊት እናቱ ደውላ ታበረታታዋለች፤ ከጨዋታ በኋላም ቢሆን የጨዋታውን ሁኔታ አስመልክቶ ከመጀመሪያዎቹ ደዋዮች አንዷ እሷ ነች።
ጎል ባስቆጠረ ቁጥር ስልክ የማውራት ምልክት የሚያሳየውም፦ “እናቴ ሆይ! ጎል አስቆጥሬአለሁና ደውይልኝ፣ ጥሪሽን እጠብቃለሁ!” የሚል ቀጥተኛ መልእክት ለእናቱ ለማስተላለፍና ላደረገችለት ቀጣይነት ያለው ውለታ ምስጋናውን ለማቅረብ ነው።
ጄሱስ በብራዚሉ ፓልሜራስ ክለብ እያለና ስሙ ገና ሳይናኝ የቀድሞ ፍቅረኛው ስልኩን የማታነሳለትና ትኩረት የማትሰጠው ነበረች።
ሆኖም በውድ ዋጋ ወደ እንግሊዙ ማንችስተር ሲቲ ከተዛወረና ስሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጠራት ከጀመረ በኋላ ደጋግማ ትደውልለት እንደነበር ይነገራል።
ጄሱስም በሜዳ ውስጥ ይህንን ምልክት በማሳየት “ቀደም ሲል ስልኬን የማታነሺው አሁን ብትደውይ ማን ያነሳልሻል?” በሚል አሽሙር መልእክት ያስተላልፍባት እንደነበር ይነገራል።
ምንም እንኳን የድሮ ፍቅረኛው ታሪክ ለደጋፊዎች አዝናኝ ወሬ ቢሆንም፣ ጋብርኤል ጄሱስ ራሱ በተደጋጋሚ እንደገለጸው የደስታው አገላለጽ ዋና ምስጢር ለእናቱ ያለው ጥልቅ ፍቅር፣ ክብርና ታማኝነት ማሳያ ነው።
ዛሬ ላይ በዓለም እግር ኳስ ትልቅ ደረጃ ላይ ቢደርስም፣ ከየት እንደመጣና ማንም በሌለበት ጊዜ ማን ከጎኑ እንደነበረች አለመርሳቱን በእያንዳንዱ ጎሉ ያስመሰክራል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የአባቱ ልጅ!
ቼልሲ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝን አስፈረመ
ማንቼስተር ዩናይትድ የመጀመሪያ ድሉን ፍለጋ ከኢፕስዊች ጋር ይፋጠጣል