የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓልን ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መስከረም 05/2019 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ በሆሳዕና ከተማ የሚገኙ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በዓሉ በከተማ ደረጃ የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 09/2019 ዓ.ም በኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ አደባባይ በድምቀት እንደሚከበርም ተጠቁሟል።
“ያሆዴ” የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በብሄሩ ተወላጆች ዘንድ አሮጌውን ዓመት በመሸኘት የክረምት ጭጋግ መውጣቱን ተከትሎ በወርሃ መስከረም የሚከበር በዓል ነው።
በዓሉም የአንድነት፣ የፍቅር፣ የመቻቻል በተለይም ተጣልተው የቆዩ ሰዎች የሚታረቁበት የዕርቅና የአብሮነት በዓል ነው።
በበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ወቅትም አባወራ ለሰንጋ መግዣ የሚሆን ገንዘብ የማዘጋጀትና ሰንጋ የመግዛት፤ እማወራ ደግሞ የቅቤ ዕቁብ(ዊጆ) በመግባት ለበዓሉ የሚሆን ቅቤ የሚታጠራቅምበት ኃላፊነት ያለው በአል ነው።
በተመሳሳይ መልኩ ወጣት ወንዶች ለበዓሉ የሚሆን የማገዶ እንጨት የመፍለጥና ደመራ የማዘጋጀት ኃላፊነት ሲኖራቸው ልጃገረዶች ደግሞ የተለያዩ ተፈጥሯዊ ቀለሞችን በመጠቀም ቤት የማስዋብና በስጋ የሚበላ ቆጮ የማዘጋጀት ሚናቸውን ይወጣሉ።
የዘንድሮ “ያሆዴ” የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 9/2019 ዓ.ም በከተማ ደረጃ ለማክበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ትንሣኤ ታደሰ ተናግረዋል።
ሆቴሎችና ሌሎች የእንግዳ ማረፊያዎች እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተለመደው የሀድያ ብሔር የእንግዳ አቀባበል ባህል ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ እንዲያስተናግዱ በሚያስችል ሁኔታ የጋራ መግባባት መፈጠሩንም ገልጸዋል።
የበዓሉ አከባበርም በተለያዩ ዝግጅቶች የታጀበ ነው ያሉት አቶ ትንሳኤ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ የባህላዊ አልባሳት የፋሽን ውድድር እና ባህላዊ አልባሳት በአንተርፕራይዞች በኩል ለሽያጭ የሚቀርቡበት መርሃ ግብር መኖሩንም ተናግረዋል።
በዓሉን በማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኒስኮ ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ሁሉም የድርሻውን ማበርከት አለበት ያሉት ኃላፊው፤ የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 09/2019 ዓ.ም በኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ አደባባይ የከተማውና የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ ከተሞች ከንቲባዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በደማቅ ስነ-ስርዓት በሚከበረው “ያሆዴ” የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ላይ ሁሉም እንዲታደሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በዓሉ በዞን ደረጃ መስከረም 12/2019 ዓ.ም በሀገር ውስጥና በወጪ የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች፣ ከአጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች፣ ከፌዴራል፣ ከክልልና ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሀዲይ ነፈራ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።
ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ጦርነቱ ሳዉዲ አረቢያ እና ሁቲ በከፈቱት የተኩስ ልውውጥ እንደ አዲስ አገርሽቷል
ያለፈውን በጀት ዓመት ተግባራት በፖሊስ ተቋምና በግለሰቦች ደረጃ በመገምገም ቀጣይ የስራ አቅጣጫን መለየት እንደሚገባ ተገለጸ
የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ በሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት የማህበረሰቡ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል እያከናወነ የሚገኘውን አበረታች ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለፁ