ጦርነቱ ሳዉዲ አረቢያ እና ሁቲ በከፈቱት የተኩስ ልውውጥ እንደ አዲስ አገርሽቷል
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ይበርዳል ተብሎ ቢጠበቅም አሁንም እንደጋለ ቀጥሏል፡፡
የዓለምን የምጣኔ ሃብት በቀጥታ ተጎጂ እንዳደረገ ጦርነት ውስጥ የገቡ አካላት ቢረዱትም የመዘዙትን ጦር ሊሰበስቡ አልቻሉም፡፡ ይባስ ብሎ ጂኦፖለቲካዊ ቅኝትን ይዞ አድማሱ ወደ መላው መካከለኛው ምስራቅ ተንሰራፍቷል፡፡
አሜሪካ እና እስራኤል፣ ኢራን እየገነባች ያለውን የኒውክሌር ግንባታ በሰላማዊ መንገድ ማቆም ባለመቻሏ አማራጫችን ጦርነት ሆኗል በሚል የከፈቱት ጦርነት ኢራንን ከግንባታዋ ሊያስቆማት አልቻለም፡፡
አሜሪካ እና እስራኤል ግን በእልከኝነት እንደ ሳዉዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ባህሬን እና ኩዌይት በመሳሰሉ ጀሌዎቻቸው ታግዘው ኢራንንና ኢራንን ያግዛሉ በሚሏቸው ቡድኖች ላይ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡
ኢራን ግን የተደበቀ ኃያልነቷን ጦርነቱን በመመከት አስመስክራለች፤ ጉዳቷ ቀላል ባይሆንም፡፡
ይህቺ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገር መገኛውን የመን ባደረገው ሁቲ፣ በፍልስጤሙ ሐማስ እና በሊባኖሱ ሂዝቦላ ታግዛ የሚደርስባትን ጥቃት በመመከት አጸፋውን እየመለሰች ትገኛለች፡፡
ይህም የጦርነቱን አድማስ ወደ የመን፣ ፍልስጤም እና ሊባኖስ አስፍቶታል፡፡
በጥቅሉ መካከለኛው ምስራቅ በዚሁ ጦርነት እየታመሰ ነው፡፡ ጉዳቱም ቢሆን ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በአውሮፓዊያኑ የካቲት 28 ቀን 2026 ጅማሮውን ካደረገ ወዲህ በተለይም ኢራንን በእጅጉ ተጎጂ አድርጓታል፡፡
ኢራን ዎር ላይቭ (Iran War Live) በድረ ገጹ እንዳሰፈረው እስከ ትናንት ድረስ (የፈረንጆቹ መስከረም 14 ቀን 2026) በጦርነቱ ከ8 ሺህ እስከ 10 ሺህ 600 ሰዎች ለሞት ሳይዳረጉ አልቀረም፡፡ የቆሰሉ ሰዎች ቁጥርም ከ50 ሺህ በላይ ነው፡፡ ከሞቱት ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በኢራን እና ሊባኖስ ሰዎች ናቸው፡፡
የጦርነቱን ዳፋ በመጀመሪያ የቀመሰችው ኢራን እስከ 6 ሺህ ሰዎች በምድሯ እንደሞቱ መረጃው ይጠቁማል፡፡ ይህ ቁጥር ቢበዛ የተባለው ነው፡፡ የሂዝቦላ ታጣቂ ቡድንን በያዘችው ሊባኖስ ደግሞ ከ4 ሺህ 300 በላይ ሰዎች በጦርነቱ መሞታቸው ነው የተነገረው፡፡ የሞቱት ሰዎች በብዛት የሀገሪቱ ዜጎች ሲሆኑ፤ የሌሎች ሀገራት ዜጎችም ይገኙበታል፡፡
ኢራን ዎር ላይቭም ሆነ አልጀዚራ እንደዘገቡት የኢራቅ 146፣ የእስራኤል 72፣ የአሜሪካ 20፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 16፣ የኦማን 14፣ የኩዌይት 12፣ የየመን 6፣ የፍልስጤም እና የሶሪያ የእያንዳንዳቸው 4፣ የሳዉዲ አረቢያ 3፣ የባህሬን 2፣ የኳታር 1 እና የፈረንሳይ ወታደር 1 ለሞት የተዳረጉ ዜጎች ናቸው፡፡
በጦርነቱ የደረሰው ጉዳት በሰዎች ሕይወትና አካል ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳቱ በጦርነቱ የተሳተፉ አካላት ለጦር መሳሪያ ያወጡት ወጪ እና የንብረት ውድመትንም ያጠቃልላል፡፡ በዚሁም መሰረት አሜሪካ እስከ ባለፈው የፈረንጆቹ ሐምሌ ወር ድረስ 37 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በቀጥታ ለጦርነቱ ፈሰስ አድርጋለች፡፡
ኢራን ደግሞ ታይም መጽሄት ይፋ እንዳደረገው 270 ቢሊየን ዶላር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወጪ አድርጋለች፡፡ የሌሎቹ በጦርነቱ የተሳተፉ ሀገራት ወጪ በይፋ አልተገለጸም፡፡
ለማንኛውም ይኸው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በአየር ላይ የድሮን ጥቃቶችን በማድረስ በሁለቱ ባላንጣ ቡድኖች መካከል እንደቀጠለ ነው፡፡ ፍራንስ 24 በትናንት ዘገባው ይፋ እንዳደረገው ጦርነቱ በሳዉዲ አረቢያ እና የመን በሚገኘው ሁቲ መካከል ተጋግሎ ቀጥሏል፡፡ ኢራን ግን በሁለቱ ግጭት ውስጥ የለሁበትም እያለች ነው፡፡
ፍራንስ 24 እንደሚለው ሳዉዲ አረቢያ በየመን ላይ ከፍተኛ የድሮን ጥቃት በመፈጸም ጉዳት አድርሳለች፡፡ ሳዉዲ በትናንትናው ዕለት ጥቃት የፈጸመችው በኢራን የሚደገፈው ሁቲ ድብደባ ከፈጸመባት ወዲህ አጸፋውን ለመመለስ እንደሆነ አስታውቃለች፡፡
ሳዉዲ በየመን ምዕራባዊ ክፍል ላይ በ24 ሰዓታት ውስጥ 54 ጊዜ ጥቃት ፈጽማለች፡፡ አስቀድሞ የሁቱ ታጣቂ ቡድን በደርዘን የሚቆጠሩ ድሮኖችንና ሚሳይሎችን የሳዉዲ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ድብደባ በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በሚገኙት ካሚስ ሙሻይት፣ አባ እና ታይፍ ከተሞች ላይ ፈጽሞ ነበር፡፡
ስሙ ያልተጠቀሰ የካሚስ ሙሻይት ነዋሪ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጸው፤ በዚሁ የሁቲ ድብደባ ለረጅም ጊዜ ከባድ ፍንዳታ ከመሰማቱም በላይ እንቅልፋቸውን መተኛት ተስኗቸው አድረዋል፡፡ 13 ንጹሃን ዜጎችም ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡
ሳዉዲ በአጸፋዋ 54 ጊዜ የፈጸመቻቸው ጥቃቶች ሁቲዎች ይገኙባቸዋል ያለቻቸው ላሂጅ፣ ቴይዝ፣ ኤልጃውፍ፣ ማሪብ እና ሃጃ አካባቢዎች ላይ ነው ድሮኖችና ሚሳይሎችን ያዘነበችው፡፡
በሁለቱ በሚለዋወጡት ጥቃት ምን ያህል ሰዎች መሞታቸው እርግጥ አይደለም፤ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ግምታቸውን ቢናገሩም፡፡ ይሁን እንጂ ግጭቱ በቀጠናው የተከሰተውን ጦርነት እንደ አዲስ ቀስቅሶታል፡፡
በዚሁ ጦርነት ምክንያት 94 ሺህ ሰዎች በየመን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ጦርነቱ በመከሰቱ በሆርሙዝ ቀጣይ ዕታ ፈንታ ዙሪያ ትናንት ሰኞ በገልፍ ሀገራት እና በኢራን መካከል ሊካሄድ የነበረው ውይይት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡ በሌላ አቅጣጫ ዛሬ ማክሰኞ ደግሞ የግብጹ ፕሬዝደንት አብድል ፈታ አልሲሲ የሳዉዲውን ልዑል ሞሃመድ ቢን ሰልማንን ተቀብለው ያነጋግራሉ ተብሎ እየተጠበቀ እንደሆነ የግብጹ ኢንዲፔንደንት በዘገባው ገልጿል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በውድቀት ላይ የሚገኘው የኢራን መንግስት በአፋጣኝ ድርድር ይፈልጋል ሲሉ በትናንትናው ዕለት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ አሜሪካም ምላሹን በቀጣይ ታስታውቃለች ብለዋል፡፡
እስከዚያው ግን የቀጠናው ጦርነት በሳዉዲ አረቢያ እና በሁቲ መካከል በሚፈጸመው የተኩስ ልውውጥ እንደ አዲስ አገርሽቶ ቀጥሏል፡፡
ዘጋቢ፡ ኢያሱ ታዴዎስ

More Stories
የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓልን ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
ያለፈውን በጀት ዓመት ተግባራት በፖሊስ ተቋምና በግለሰቦች ደረጃ በመገምገም ቀጣይ የስራ አቅጣጫን መለየት እንደሚገባ ተገለጸ
የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ በሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት የማህበረሰቡ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል እያከናወነ የሚገኘውን አበረታች ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለፁ