ማንቼስተር ዩናይትድ በዝውውር ገበያው አዳዲስ አማራጮችን እየተመለከተ ነው

ማንቼስተር ዩናይትድ በዝውውር ገበያው አዳዲስ አማራጮችን እየተመለከተ ነው

ማንቸስተር ዩናይትድ የክረምቱን የዝውውር መስኮት ተጠቅሞ ቡድኑን ለማጠናከር ባለው ዕቅድ መሠረት በተለያዩ የሜዳ ክፍሎች ላይ ኢላማ ያደረገባቸውን ለማምጣት እየተዘጋጀ ይገኛል።

ክለቡ በግራ መስመር ተከላካይ ሥፍራ ላይ አዲስ ተጫዋች ለማስፈረም ውሳኔ ላይ ከደረሰ፣ የኒውካስል ዩናይትዱ ሊዊስ ሃል በዋናነት ከተያዙት እጩዎች መካከል አንዱ ሆኖ ቀጥሏል።

ዩናይትድ የተጫዋቹን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ ይገኛል።

በሌላ በኩል ዩናይትድ የቦርንመዙን አማካይ አሌክስ ስኮትን ለማስፈረም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ቢሠራም፣ ተጫዋቹን ለማስፈረም የቅድመ ግምት የበላይነቱን የያዘው ቼልሲ መሆኑን ዘ አትሌቲክ አስነብቧል።

ቼልሲ ቀደም ሲል ለ22 ዓመቱ እንግሊዛዊ አማካይ ያቀረበው 64 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ በቦርንመዝ ውድቅ ተደርጎበታል።

ቦርንመዝ በበኩሉ ተጫዋቹ “ለሽያጭ አይቀርብም” የሚል ጽኑ አቋም ቢይዝም፣ ስኮት የሚሸጥ ከሆነ ግን ቀጣይ ማረፊያው ስታምፎርድ ብሪጅ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል።

በፊት መስመር በኩል ማንቼስተር ዩናይትድ ከቤንጃሚን ሴስኮ ጋር የፊት መስመር የግብ ማደንን ኃላፊነት የሚጋራ አጥቂ ፍለጋ ላይ ይገኛል።

ዩናይትድ በ2024 እና 2025 የቀድሞ አጥቂው ዴኒ ዌልቤክን ከብራይተን ለመመለስ ንግግሮችን አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመትም ሂደቱ እስከ መጨረሻ ደረጃ ደርሶ ነበር።

ሆኖም ማንቼስተር ዩናይትድ እስካሁን ድረስ ለ35 ዓመቱ አጥቂ እንደገና ጥያቄ ለማቅረብ ምንም ዓይነት ፍላጎት አላሳየም።

በአሁኑ ወቅት ዌልቤክ በቼልሲ የዝውውር ዕቅድ ውስጥ ገብቶ ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ ታውቋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ