የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ እና የግብርና ቴክኖሎጂን በተገቢ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ምርትና ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን በከምባታ ዞን የዶዮገና ወረዳ አንዳንድ አርሶ አደሮች ተናገሩ

የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ እና የግብርና ቴክኖሎጂን በተገቢ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ምርትና ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን በከምባታ ዞን የዶዮገና ወረዳ አንዳንድ አርሶ አደሮች ተናገሩ

‎በዞኑ ዶዮገና ወረዳ አመቾ ዋቶ ቀበሌ አዶዬ የስንዴ ክላስተር የ2018/19 የምርት ዘመን የመኸር እርሻ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሂዷል።


መርሀ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የከምባታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ሔራሞ እንደገለጹት፤ ለግብርናው ዘርፍ መንግስት በሰጠው ትኩረት ዘርፈ ብዙ ለውጥ እየተመዘገበ በመምጣቱ የአርሶ አደሩ የኢኮኖሚ አቅም እየተለወጠ መጥቷል።


ከለውጡ መንግስት በኋላ የሀገራችን ኢኮኖሚ ግብርና ላይ ከተንጠለጠለበት ወደ ብዝኃ ዘርፍ መሸጋገር ችሏል ያሉት ኃላፊው፤ ‎የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ አነስተኛ ማሳዎችን በማቀናጀት ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በመጠቀም ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ህይወት ከመቀየር ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።


‎በዞኑ 30 ሺ 457 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተሾመ፤ አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርና ግብዓትን አሟልቶ ከመጠቀም ባሻገር ሰብሉን ከተባይና በሽታ አደጋ ለመጠበቅ የሚያስችል ተከታታይ የክትትልና የእንክብካቤ ሥራ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።


አርሶ አደሩ በግብርና ስራ ከማሳ ዝግጅት አንስቶ እስከ ምርት ውቅያ ድረስ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

‎የዶዮገና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየለ ጋርከቦ በበኩላቸው ሀገራችን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንዲቻል መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አንስተው ለዚህም የአዶዬ ክላስተር አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

‎አርሶ አደሩ በባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ የሚታዩበትን የክህሎት ክፍተቶች በባለሙያዎች በመሙላት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


‎የ‎አዶዬ ክላስተር አርሶ አደሮች በማኅበር ተደራጅተውና ማሳቸውን አቀናጅተው በመሥራት ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ የሚገኝ የተሞክሮ ማዕከል መሆኑንም አቶ አየለ አክለዋል።


የለውጡ መንግስት የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ከጀመረ ወዲህ የበርካታ አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ አቅም ለውጥ እያስመዘገበ ከመምጣቱም ባለፈ የአርሶ አደሩ ግንዛቤ እየጨመረ መምጣቱን የወረዳው ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ዘርሁን ሁሴን ተናግረዋል።


‎የአዶዬ ክላስተር አርሶ አደሮች በበኩላቸው፤ ‎የኩታ ገጠም አስተራረስና የግብርና ቴክኖሎጂን በተገቢ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ምርትና ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን በመጠቆም በኩታ ገጠም የእርሻ ስራ በቅንጅት በመሥራት አበረታች ለውጦችን እያስመዘግቡ መሆኑን ተናግረዋል።


‎በዶዮገና ወረዳ በአመቾ ዋቶ ቀበሌ አደዬ የስንዴ ክላስተር 92 አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ስራ እየተሳተፉ ያሉ ሲሆን በአጠቃላይ 62 ሄክታር ማሳ እንደሚለማም ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።


ዘጋቢ: መልካሙ ታፈሰ – ከሆሳዕና ጣቢያችን