የ2018 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ታላላቅ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት እና የዲጂታል ሽግግር የሉዓላዊነቷ ምሰሶ መሆን የቻለችበት አመት መሆኑን አቶ አልማው ዘውዴ ገለፁ

የ2018 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ታላላቅ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት እና የዲጂታል ሽግግር የሉዓላዊነቷ ምሰሶ መሆን የቻለችበት አመት መሆኑን አቶ አልማው ዘውዴ ገለፁ

ጳጉሜን 5 የነገ ቀን በዓል ክልላዊ መድረክ በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ በተለያዩ ሁነቶች በደማቅ ስነ-ስርዓት ተከብራል።

በመርሃ ግብሩ በክብር እንግድነት የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ እንደተናገሩት፤ ጳጉሜ ወር ካለፈው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት የምንሻገርባት፣ የክረምቱ ማብቂያና የብርሃን መውጫ የምናይባት ልዩ የወራት ድልድይ እና ያለፈውን ጊዜ የምንሸኝባት የነገ ቀንን በብሩህ ምናብ የምንመለከትባት ልዩ ወራት ናት።

ጳጉሜን 5 የነገ ቀን በሚል ስያሜ መከበሩ ዲጂታላይዜሽን ለነገዋ ኢትዮጵያ ግንባታ እና ሉዓላዊነት መከበር ሀገራችን ወደ ዲጂታላይዜሽን ሽግግር ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ለማብሰር መሆኑን ገልፀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ካሁን በኋላ የሌሎችን እጅ የማታይ በቴክኖሎጂ ሽግግር ቀደሚ መሆን የምትችል መሆኗን ተናግረዋል።

የሀገራችን ኢትዮጵያ እድገት በአምስት ዘርፎች በተጀመሩ መሠረቶች ተገንብታ አሁን ላይ ትልቅ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የዲጂታል ፖሊሲን ስትራቴጂ የምትከተል ሀገር መሆኗን ገልፀው አለም ላይ ያሉ ስትራቴጂዎችን ቀድማ እየተከተለች ያለች ሀገር መሆኗን ገልፀዋል።

በሌላ ዓለም ላይ የአለም ነበራዊ ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች በቴክኖሎጂ ታግዛ ከአለም ጋር አኩል ለመሆን እየተጋች ያለች ናት ብለዋል።

የዲጂታል አቅምን ለማፋጠን እያንዳንዱ ማህበረሰብ ራሱን የሚገልፅ የዲጂታል መታወቂያ በመያዝ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ማግኘት አንዳለበት አቶ ሀብታሙ ገልፀው፤ በቀጣይ ሁሉም ማህበረሰብ የዲጂታል ዓለምን መቀላቀል አለበት ብለዋል።

የዛሬውን የነገ ቀን አስመልክቶ ሰነድ በክልሉ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘመድኩን ሰለሞን ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በማጠቃለያ መድረኩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፣ የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን፣ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ለዊን ጨምሮ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን ዳጉሳ – ከሚዛን ጣቢያችን