ህዝበ ክርስቲያኑ የ2019 ዓ.ም የእንቁጣጣሽ በዓልን በሚያከብርበት ወቅት አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሀይማኖት አባቶች ተናገሩ

የሃይማኖት አባቶቹ አዲሱ ዓመት የሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነቷ ጎልቶ የሚታይበት የድል ዓመት እንዲሆን በመመኘት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሃይመኖት ተቋማት ፎረም ሰብሳቢና የሙዱላ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን መሪዎች ሰብሳቢ አቶ አየለ አሼቦ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠምባሮ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የሙዱላ ደብረ ሰላም ቅዱሰ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መልዓከ ሰላም ቀሲስ ብርሃኑ እልታሞ፤ የእንቁጣጣሽ በዓል አሮጌውን 2018 አመት በመሻገር ወደ አዲሱ ዓመት የተሻገርንበት በመሆኑ ቤተክርስቲያን ላለፈው ጊዜ በማመስገን ለቀጣዩ ዓመት ደግሞ ለእግዚአብሔር አደራ የሚትሰጥበት በዓል እንደመሆኑ መጠን ምዕመናን ከመብልና ከመጠጥ ባሻገር መልካምነትን በመገንዘብ ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንደ ሙዱላ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ለአቅመ ደካሞች፣ ለወላጅ አጥ ህፃናትና ድጋፍ ለሚሹ አካላት ዓመት በዓሉን ምክንያት በማድረግ አስቀድመው ድጋፍ ማድረገቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠምባሮ ወረዳ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሊቃ ህሩያን መምህር አመነ ህምበጎ እና የሙዱላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጸሐፊ ሲሳይ በቀለ፤ የእንቁጣጣሽ በዓል በቤተክርስቲያኒቱ በድምቀት ከሚከበሩ ዓቢይ በዓላት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው በአስተምሮቱ መሰረት በተለያዩ መንፈሳዊ ክዋኔዎች እንደሚያከብሩ ገልፀዋል።

የሀይማኖት አባቶቹ አክለውም፤ ህዝበ ክርስቲያኑ የእንቁጣጣሽ በዓልን በሚያከብርበት ወቅት አቅመ ደካሞችን፣ ወላጅ አጥ ህፃናትንና የሚረዳቸው አካል የሌላቸውን በመደገፍ ያለውን በማካፈል፣ አብሮ በመብላት በደስታ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመጨረሻም 2019 አዲሱ ዓመት የሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነቷ ጎልቶ የሚታይበት የድልና የብልጽግና ዓመት እንዲሆን በመመኘት ለመላው ህብረተሰብ በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ: ሙሉነሽ ለማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን