ብሔራዊ የዲጂታል ፋይዳ መታወቂያ መያዝ የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት እንደሚጠቅም ተገለጸ
በጌዴኦ ዞን የ2018 በጀት ዓመት ብሔራዊ የዲጂታል ፋይዳ መታወቂያ አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ንቅናቄ መድረክ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።
ብሔራዊ የዲጂታል ፋይዳ መታወቂያ ከ5 ዓመት በላይ ዕድሜ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሁሉ ወሳኝነት እንዳለው ተመላክቷል።
የንቅናቄ መድረኩን በውይይት የከፈቱት የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኝ ታደሰ፤ ህዝቡን ለፋይዳ መታወቂያ ስንመዘግብ ቀድሞ መግባባትና ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅብናል ብለዋል።
አክለውም ከማኑዋል ወደ ዲጂታል ሲስተም ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻቸውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የጌዴኦ ዞን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረጀ ሾንጣ፤ በሁሉም የአገልግሎት ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።
ለፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ ኢትዮ ቴሌ፣ ፖስታ ቤትና የንግድ ባንክ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም አቶ ደረጀ አስገንዝበዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል ዶ/ር ዳዊት ጀቦ፣ አቶ አብርሃም መኩሪያ እና ሌሎች ከህብረተሰቡ በመግባባት ሲሠሩ መቆየታቸውን በመግለጽ የመመዝገቢያ ኪት ችግር እንደነበረም አስታውቀዋል።
ለ2019 በጀት ዓመት አፈጻጸም ህብረተሰቡ በስፋት በሚገኝባቸው አካባቢዎች የግንዛቤ ሥራ በመሥራት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
ህዝበ ክርስቲያኑ የ2019 ዓ.ም የእንቁጣጣሽ በዓልን በሚያከብርበት ወቅት አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሀይማኖት አባቶች ተናገሩ
የ2018 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ታላላቅ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት እና የዲጂታል ሽግግር የሉዓላዊነቷ ምሰሶ መሆን የቻለችበት አመት መሆኑን አቶ አልማው ዘውዴ ገለፁ
ጳጕሜን 5 “የነገው ቀን” በኮሬ ዞን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው