ዚነዲን ዚዳን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ
የቀድሞው የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ እና የፈረንሳይ ታሪካዊ ተጫዋች ዚነዲን ዚዳን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ በይፋ መሾሙ ተረጋግጧል።
የ54 ዓመቱ ዚዳን ኃላፊነቱን የተረከበው ለ14 ዓመታት ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ሲመሩ የቆዩትን ዲዲዬ ዴሻምፕን በመተካት ነው።
ዴሻምፕ ቡድናቸውን በ2026 የዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ማድረስ ቢችሉም፣ በስፔን ተሸንፈው በአራተኛ ደረጃ ውድድራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ተገደዋል።
ዚዳን ሀገሩን እስከ 2030 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ድረስ የሚያቆየውን የኮንትራት ውል የፈረመ ሲሆን፤ የመጀመርያ ይፋዊ ጨዋታውን በመስከረም ወር በኔሽንስ ሊግ ከቱርክ ጋር በሚደረገው ጨዋታ ያደርጋል።
የ2028 የአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያም ቀጣዩ ትልቅ ፈተናው ይሆናል።
ከሹመቱ በኋላ አስተያየቱን የሰጠው ዚዳን፤ የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን ማሰልጠን ታላቅ ኩራት እንደሆነ ገልጿል።
“ይህን ሁልጊዜም እናገረዋለሁ፤ ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የሚበልጥ ምንም ታላቅ ነገር የለም” ያለው ዚዳን“የዚህ ታላቅ ቡድን አሰልጣኝ መሆን ትልቅ ደስታ እና ኩራት ነው። በቡድኑ ከፍተኛ እቅድ እና ትልቅ አላማ አለኝ“ ብሏል።
ዚዳን አክሎም ለቀድሞው አሰልጣኝ ዲዲዬ ዴሻምፕ እና ለስራ ባልደረቦቹ ለ14 ዓመታት ላበረከቱት ታላቅ አገልግሎት ምስጋናውን አቅርቧል።
የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፊሊፕ ዲያሎ በበኩላቸው፤ ዚዳንን “ታሪካዊ የእግርኳስ ሰው” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፤ የዚዳን መሾም ለሀገሪቱ እግር ኳስ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት እና ከፍተኛ ስኬት እንደሚያስመዘግብ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በ1998 ፈረንሳይ የዓለም ዋንጫን ስታነሳ የቡድኑ ዋና ኮከብ የነበረው ዚዳን፤ እ.ኤ.አ በ2006 ከተጫዋችነት ከተገለለ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት የተቀላቀለው እ.ኤ.አ በ2014 የሪያል ማድሪድ ቢ (ካስቲያ) ቡድንን በመያዝ ነበር።
በ2016 የሪያል ማድሪድ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ከተሾመ በኋላ አስደናቂ የታሪክ ማህደር አስመዝግቧል።
በተለይም ሪያል ማድሪድን በመምራት ተከታታይ ሶስት የካምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን (ከ2016 እስከ 2018) በማንሳት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ተከታታይ ሶስት ጊዜ ያሸነፈ የመጀመሪያው አሰልጣኝ ሆኗል።
በ2016-17 እና በሁለተኛው የአሰልጣኝነት ዘመኑ በ2019-20 የስፔን ላሊጋ ሻምፒዮን መሆን ችሏል።
በ2021 ከሪያል ማድሪድ ከተለያየ በኋላ ከማንኛውም የአሰልጣኝነት ስራ ርቆ የቆየው ዚዳን፤ ከዓመታት ቆይታ በኋላ የደጋፊዎች እና የፌዴሬሽኑ ጥረት በመጨረሻ የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን የመምራት ህልሙን አሳክቷል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
ዚነዲን ዚዳን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ

More Stories
ሪዮ ፈርዲናንድ ዳኒ ዌልቤክ ቼልሲን ትቶ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ እንዲመለስ ጥሪ አቀረበ
አርሰናል ቪኒሺዬስ ጁኒየርን ለማስፈረም ሁኔታዎችን እየተከታተለ ነው
በ22 ዓመቱ 7ኛ ክለቡን የተቀላቀለው ጆን ዱራን