ሪዮ ፈርዲናንድ ዳኒ ዌልቤክ ቼልሲን ትቶ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ እንዲመለስ ጥሪ አቀረበ

ሪዮ ፈርዲናንድ ዳኒ ዌልቤክ ቼልሲን ትቶ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ እንዲመለስ ጥሪ አቀረበ

የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ የኋላ ደጀን የነበረው ሪዮ ፈርዲናንድ፤ የብራይተኑ አጥቂ ዳኒ ዌልቤክ ወደ ቼልሲ ለመዛወር የሚያደረገውን ጥረት በመተው ወደ ቀድሞ ክለቡ ማንችስተር ዩናይትድ እንዲመለስ ጥሪ አቅርቧል።

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ከ35 ዓመቱ አጥቂ ጋር አወንታዊ የሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ውይይቶችን ማድረጉ ቢነገርም፣ ፈርዲናንድ ግን በማህበራዊ ሚዲያ ገፁ ባስተላለፈው መልዕክት ዌልቤክ የቼልሲን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ወደ ልጅነት ክለቡ ዩናይትድ ሊመለስ እንደሚገባ አሳስቧል።

ዳኒ ዌልቤክ በማንችስተር ዩናይትድ ታዳጊዎች አካዳሚ ያደገ ሲሆን፤ በቀያይ ሰይጣኖቹ ቤት በነበረው ቆይታ ለዋናው ቡድን በ142 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 29 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

አጥቂው እ.ኤ.አ በ2014 ኦልድ ትራፎርድን ለቆ ወደ አርሰናል ማመራቱ ይታወሳል።

አሁን ላይ በብራይተን የሚገኘው ዌልቤክ በክረምቱ የዝውውር መስኮት በቼልሲ መፈለጉ የበርካቶችን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ሳለ የፈርዲናንድ ጥሪ ደግሞ የዩናይትድ ደጋፊዎችን ትኩረት ስቧል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ