በክረምት የወጣቶች በጎ ተግባር ከ34 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ በ15 የተለያዩ መስኮች በጎ ተግባራትን ለማከናወን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

በክረምት የወጣቶች በጎ ተግባር ከ34 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ በ15 የተለያዩ መስኮች በጎ ተግባራትን ለማከናወን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2018 የክረምት የወጣቶች በጎ ተግባር ከ34 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ በ15 የተለያዩ መስኮች በጎ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ በሀላባ ዞን የዌራ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት አስታወቀ::

በወጣቶች የበጎ ፍቃድ ተግባር ከ93 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስትን ወጪ ለማዳን ስለመታቀዱም ተጠቁሟል::

በዚህ ክረምት ከ34 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የወጣቶች በጎ ተግባር እንቅስቃሴ መኖሩን የገለጹት በሀላባ ዞን የዌራ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ በርገና ጡሚሶ ናቸው::

በዚህም አቅመ ደካሞችን መርዳት፣ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማሄድ፣ የደም ልገሳ፣ የመንገድ ጥገና፣ የክረምት ትምህርት ፕሮግራምን ጨምሮ በጥቅሉ በ15 መስኮች የሚከናወኑ በጎ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውንም አቶ በርገና ጠቁመዋል::

የበጎ ተግባር ዘመቻው ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ የወጣቶች የነቃ ተሣትፎ ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ምክትል ኃላፊው፥ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለአቅመ ደካሞች ከ9 በላይ ቤቶች ተገንብተዋል ብለዋል::

ለአቅመ ደካሞች መጠለያ ቤት ገንብቶ ከመስጠት ባሻገር ለህይወታቸው መቋቋሚያነት የሚውል የዶሮና ሌሎች የርቢ እንስሳት እንዲያረቡ አስከማመቻቸት ድረስ እየተሰራ ስለመሆኑም ገልፀዋል::

አቶ በርገና አክለውም በዘንድሮው የክረምት ወጣቶች በጎ ተግባር ከ93 ሚሊዮን ብር በላይ ከመንግስት ሊወጣ የሚችለውን ወጪ ለማትረፍ መታቀዱንም አስታውቀዋል::

ወጣቶች ያላቸውን የክረምት ጊዜያቸውን በተለያዩ በጎ ተግባራት ሊያሳልፉ እንደሚገባም ምክትል ኃላፊው አሳስበዋል::

በወረዳው ያነጋገርናቸው የበጎ ተግባር ተሣታፊዎች እንደገለፁት በጎ ተግባር የለምንም ክፍያ በሰዎች መልካም ፍቃድ ብቻ የሚከወን መልካም ተግባር መሆኑን ጠቁመው፥ በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል::

ዘጋቢ: አብዱልሰመድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን