የዳሽን ባንክ ሀዋሳ ዲስትሪክት ሰራተኞች “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አከናወኑ

የዳሽን ባንክ ሀዋሳ ዲስትሪክት ሰራተኞች “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አከናወኑ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዳሽን ባንክ ሀዋሳ ዲስትሪክት አመራሮች እና ሰራተኞች በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያለባቸውን ማህበራዊ ሀላፊነት ለመወጣት በታቦር ተራራ ላይ በመገኘት የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር አካሂደዋል።

ይህ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በክረምት ወቅት እየተተገበሩ ከሚገኙና ተስፋን እንትከል ከሚለው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መሪ ቃል ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ባንኩ ይህን መርሀ ግብር ማካሄዱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ እና ነገን ብሩህ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የዳሽን ባንክ ሀዋሳ ዲስትሪክት ቢዝነስ ዳይሬክተር አቶ አስናቀ ደምሴ፣ የዲስትሪክቱ የቀጠና ቢዝነስ ማኔጀር ወ/ሮ ሮዛ ተከተል እንዲሁም አቶ መሀመድኑር ፈዪዳ የቀጠናው ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ማኔጀር በስፍራው ተገኝተው አሻራቸውን ማኖር በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

ኃላፊዎቹ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዳሽን ባንክ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በዲስትሪክቱ ደረጃ ለአምስተኛ ዙር መካሄዱን አስታውሰዋል።

ቀደም ሲል በተከታታይ በተካሄዱት አራት ዙሮች የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ረገድ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን የገለጹት ኃላፊዎቹ፤ ዘንድሮ የተተከሉት ችግኞች የመጽደቅ መጠናቸው እንዲጨምር ባንኩ አስፈላጊውን ክትትልና እንክብካቤ ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የባንኩ ሠራተኞች በበኩላቸው፤ ለአምስት ተከታታይ ዙሮች በዚህ ሀገራዊና አካባቢያዊ ፋይዳ ባለው የልማት ሥራ ላይ በመሳተፍ አረንጓዴ አሻራቸውን ማሳረፍ በመቻላቸው የተሰማቸውን ኩራትና ደስታ ገልጸው፣ በቀጣይም ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የተፈጥሮ ደንና ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ደሞዜ አርገቶ በበኩላቸው፤ ከዳሽን ባንድ አመራሮች እና ሰራተኞች ጋር በጋራ በመሆን አሻራቸውን ማሳረፍ መቻላቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀው በከተማው መስል ተግባራትን ከሚተገብሩ አካላት ጋር በጋራ የመስራት ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጡ አፅንኦት ሰተዋል።

ሀላፊው አክለውም ከችግኝ ጋር ተስፋን በመትከል ለመጪው ትውልድ ብሩህ የሆነች ሀገርን ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዛሬው እለት በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብርም ከ 2000 በላይ የሚሆኑ ለጥላ እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ችግኞችን በመትከል እና ችግኞቹን ለመንከባከብ ቃል በመግባት መርሀ ግብሩ በተሳካ ሁኔታ ጠተናቋል።

ዘጋቢ፡ ሸዊት ሂርጶ