በ22 ዓመቱ 7ኛ ክለቡን የተቀላቀለው ጆን ዱራን

በ22 ዓመቱ 7ኛ ክለቡን የተቀላቀለው ጆን ዱራን

በእግር ኳሱ ዓለም ሙሉ የጨዋታ ዘመናቸውን በአንድ ክለብ ብቻ በመጫወት የታማኝነት ተምሳሌት የሆኑ ብዙ ተጫዋቾች አሉ።

ለአብነትም የፕሪሚየር ሊጉ የበርካታ ዋንጫዎች ባለቤት ሪያን ጊግስ (ማንችስተር ዩናይትድ)፣ የኤሲ ሚላኑ ታሪካዊው ተጫዋች ፓኦሎ ማልዲኒ፣ የሮማው ንጉሥ ፍራንቸስኮ ቶቲ እና የአርሰናሉ የኋላ ደጀን ቶኒ አዳምስ የዚሁ አቋም ማረጋገጫዎች ናቸው።

በአሁኑ ትውልድም ቢሆን እንደ ቡካዮ ሳካ (አርሰናል) እና ፊል ፎደን (ማንችስተር ሲቲ) ያሉ ኮከቦች ይህንን የክለብ ታማኝነት አሰረ-ፍኖት ይከተላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ነገር ግን ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ በወጣትነታቸው የበርካታ ክለቦችን ማሊያ በመቀያየር «የጉዞ አበጋዝ» የሚል ስም የሚያተርፉ ተጫዋቾች አልጠፉም።

የዚህ ማረጋገጫ ደግሞ የቀድሞው የአስቶን ቪላ አጥቂ ጆን ዱራን ነው።

ኮሎምቢያዊው አጥቂ በ22 ዓመቱ በቅርቡ ከሳኡዲው አል-ናስር በውሰት ወደ ፖርቱጋሉ ቤንፊካ በማቅናት በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቱ 7ኛ ክለቡን ተቀላቅሏል።

ጆን ዱራን እስካሁን ለሀገሩ ክለብ ኤንቪጋዶ፣ ለአሜሪካው ቺካጎ ፋየር፣ ለእንግሊዙ አስቶን ቪላ፣ ለሳውዲው አል-ናስር ፣ ለቱርኩ ፌነርባቼ ፣ ለሩሲያው ዜኒት ሴንት ፒተርስበርግ እንዲሁም ለፖርቹጋሉ ቤንፊካ በቋሚነት አሊያም በውሰት ፊርማውን አኑሯል።

ዱራን በ23 ዓመት ልደቱ ዋዜማ 7 የተለያዩ ክለቦችን እና 7 ሀገራትን በማቋረጥ የዘመናችን ልዩ የወጣትነት ጉዞ አስመዝግቧል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ