የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ ከፍተኛ የመንፈስ እርካታ የሚያጎናጽፍ ተግባር በመሆኑ ተግባሩን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑሪዬ(ዶ/ር) ገለፁ
ይህ የተገለፀው “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መርህ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወልቂጤ ክላስተር የክልል ተቋማት አመራሮች በጉራጌ ዞን አገና ከተማ አስተዳደር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑሪዬ(ዶ/ር) የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በጉራጌ ዞን አገና ከተማ ባስጀመሩት ወቅት እንደገለፁት፤ የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ ከፍተኛ የመንፈስ እርካታ የሚያጎናጽፍ ተግባር በመሆኑ ተግባሩን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።
በተለይም የክረምት ወራት ኢትዮጵያውያን በጎ ተግባራት በስፋት የሚያከናውኑበት ወቅት በመሆኑ ወጣቶች ከአቅመ ደካማ ወገኖቻቸው ጎን በመቆም የመደጋገፍና የመተሳሰብ እሴቶችን ማጎልበት ይገባቸዋል ብለዋል።
በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ በሚል መርህ በሀገር ደረጃ እየተተገበረ ያለው ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል ዶ/ር መሀመድ።
የአገና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀምዱ ዘርጋ በበኩላቸው፤ የብልፅግና ፓርቲ ልዩ መግለጫ የሆነው ሰው ተኮር ተግባር በከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በወልቂጤ ክላስተር የክልል ተቋማት እና በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት አማካኝነት በአገና ከተማ ነዋሪ ለሆኑት አቅመ ደካማና ጧሪ ደጋፊ ለሌላቸው አንዲት እናት ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤት ግንባታ በማስጀመራቸው አመስግነዋል።
በጉራጌ ዞን አገና ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ ዝንወት አሶሬ እንደተናገሩት፤ አቅመ ደካማና ጧሪም ደጋፊም የሌላቸው ከመሆኑ የተነሳ በፈራረሰ ቤት በጋ ፀሀይ ክረምት ደግሞ ዝናብ ይፈራረቅባቸው እንደነበረ ገልፀው መንግስት ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የወ/ሮ ዝንወት አሶሬ ጎረቤት የሆኑት አቶ ወልዴ ግርማ፤ ግለሰቧ በተጎሳቆለ ቤት በርካታ ችግሮች ተቋቁመው ይኖሩ እንደነበረ ምስክርነቱ የሰጠ ሲሆን መንግስት ባደረገው መልካም ተግባር መደሰታቸውን ተናግሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ እና የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ናስር ሀሰንን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የአገና ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች በአገና አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
ዘጋቢ፡ ምትኬ ገ/ወልድ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጉራጌ ዞን አገና ከተማ ተጀመረ
የክረምት ጊዜያቸውን ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ ባላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ማዋላቸው ደስታ እንደፈጠረላቸው የሆሳዕና ከተማ ወጣቶች ተናገሩ
ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በተሰረው ስራ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ