ፔፕ ጓርዲዮላ የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ጥሪን ውድቅ አደረጉ
የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ የጣሊያን ብሔራዊ ቡድንን የመረከብ እድልን ውድቅ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ጣሊያን ለ2026 ዓ.ዓ የዓለም ዋንጫ ሳታልፍ መቅረቷን ተከተሎ አሰልጣኝ ጄናሮ ጋቱሶ ከሃላፊነታቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።
የጣሊያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒካል ዳይሬክተር ፓኦሎ ማልዲኒ እና የፌዴሬሽኑ ሃላፊ ጆቫኒ ማላጎ እንደተናገሩት፡ ፌዴሬሽኑ ጋቱሶን በሚተኩ አሰልጣኞች ዙሪያ ከጓርዲዮላ ጋር ውይይት አድርጎ ነበር።
ሆኖም ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደጠቆሙት፡ ከስፔናዊው አሰልጣኝ ጋር የተደረገው ንግግር ወደፊት ሊገፋ ስላልቻለ ጓርዲዮላ የቀረበላቸውን ጥሪ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ጣሊያን በዓለም እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ ስም ያላቸውን አሰልጣኞች ለማምጣት ባቀደችው “ታላቅ ፕሮጀክት” መሰረት፡ ማልዲኒ ከጓርዲዮላ በተጨማሪ ከወቅቱ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ጋርም ንግግር ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።
አንቼሎቲ ከብራዚል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር እስከ 2030 የሚያቆይ ኮንትራት አላቸው።
ፔፕ ጓርዲዮላ በ2025-26 የውድድር ዘመን ማጠቃለያ ላይ ከ10 ዓመታት ስኬታማ የሲቲ ቆይታ በኋላ ከክሉቡ መለያየታቸው ይታወሳል።
በሲቲ ቆይታቸው 6 የፕሪሚየር ሊግ፣ 3 ኤፍኤ ካፕ፣ 5 ካራባኦ ካፕ እና የ2023 የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አንስተዋል።
ከዚህ ቀደም ባርሴሎናን እና ባየር ሙኒክን ያሰለጠኑት ጓርዲዮላ፡ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ አሰልጣኝ ሆነው ሰርተው አያውቁም።
አራት ጊዜ የዓለም ቻምፒዮን የሆነችው ጣሊያን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና በመለያ ፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ ሆናለች።
ይህን ተከተሎ አሰልጣኝ ጋቱሶ፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ገብርኤል ግራቪና እና የልኡካን ቡድኑ መሪ ጃንሉኢጂ ቡፎን ከሃላፊነታቸው ለቀዋል።
አዙሪዎች (ጣሊያኖች) ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ሲሳናቸው ለተከታታይ ሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፡ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ዓ ዋንጫውን ካነሱ ወዲህ ከምድብ ጨዋታ ማለፍ አልቻሉም።
ሆኖም በሮቤርቶ ማልቺኒ ይመሩ በነበረበት ወቅት የ2020 የአውሮፓ ሻምፒዮና (ዩሮ) አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።
ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ
ፔፕ ጓርዲዮላ የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ጥሪን ውድቅ አደረጉ

More Stories
ሮድሪ የፊታችን ሰኞ ቀዶ ጥገና ያደርጋል
ዶናልድ ትራምፕ ጂያኒ ኢንፋንቲኖን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ማድረግ ይፈልጋሉ
ዊሊያም ሳሊባ በጉዳት ምክንያት ለረዥም ጊዜ ከሜዳ ይርቃል