ዶናልድ ትራምፕ ጂያኒ ኢንፋንቲኖን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ማድረግ ይፈልጋሉ
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንት የሆኑትን ጂያኒ ኢንፋንቲኖን የሚቀጥለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አድርገው ለመሾም ፍላጎት እንዳላቸው ዘገባዎች አመላከቱ።
በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አዘጋጅነት ከተካሄደው የ2026 ዓለም ዋንጫ ጋር ተያይዞ ሁለቱ መሪዎች ያሳዩት ቅርበት ወደ ፖለቲካዊ አጋርነት እያደገ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ትራምፕ ኢንፋንቲኖ «በዓለም ዙሪያ በሁሉም አካላት የተከበሩና ሰዎችን በአንድነት የማስተባበር ልዩ ክህሎት ያላቸው ሰው ናቸው» በሚል ማሞገሳቸውን ኒው ዮርክ ፖስት የፕሬዚዳንቱን ቅርብ ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።
ዕድሜያቸው 56 የሆኑት ስዊዘርላንዳዊው የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የነበራቸው ወዳጅነት የጀመረው አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2018 የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ ባቀረበችበት ወቅት ነበር።
በተለይም በቅርብ ጊዜያት ሁለቱ መሪዎች ያሳዩት የጠበቀ ግንኙነት በርካታ ክስተቶችን አስተናግዷል።
ኢንፋንቲኖ ባለፈው ታህሳስ ወር ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት ሳያገኙ ቀርተዋል በተባለበት ወቅት የመጀመሪያውን የፊፋ የሰላም ሽልማት (FIFA Peace Prize) ለትራምፕ አበርክተውላቸዋል።
የሰብዓዊ መብት ተከራካሪው ‘ፌር ስኩዌር’ (Fair Square) የተሰኘው ድርጅት ኢንፋንቲኖ የፊፋን የፖለቲካ ገለልተኝነት ሕግ በመጣስ የትራምፕን ፖሊሲዎች በግልጽ ደግፈዋል በሚል በፊፋ የስነ-ምግባር ኮሚቴ ዘንድ አቤቱታ አቅርቦባቸው ነበር።
በቅርቡ በዓለም ዋንጫ ወቅት የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ፎላሪን ባሎገን የተሰጠበት የቀይ ካርድ እገዳ በትራምፕ ጣልቃ ገብነት በፊፋ መሻሩ በስፖርቱ ዓለም ትልቅ ቅሬታና ትችት አስነስቶ ነበር።
ኢንፋንቲኖ በትራምፕ «የሰላም ቦርድ» ስብሰባ ላይ በመገኘት በጋዛ ለአዲስ ስታዲየም እና እግር ኳስ አካዳሚ ግንባታ የሚሆን የ7 ቢሊዮን ዶላር የረድኤት ፓኬጅ ቃል የገቡ ሲሆን፣ በዓለም ዋንጫ እጣ ድልድል ወቅትም ለትራምፕ ስማቸው የተቀረጸበት ወርቃማ ዋንጫና ሜዳሊያ አበርክተውላቸዋል።
በአሁኑ ወቅት የተመድ ዋና ጸሐፊ የሆኑት አንቶኒዮ ጉተሬዝ በታህሳስ ወር ላይ የሥልጣን ዘመናቸውን ያጠናቅቃሉ።
ኢንፋንቲኖ ቦታውን ለመረከብ የዶናልድ ትራምፕን ድጋፍ ቢያገኙ እንኳ ሂደቱ ጥብቅ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች አሉት።
ዕጩው በመጀመሪያ በ15 አባላት ባሉት የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ድጋፍ ማግኘት አለበት (የትኛውም ቪቶ ድምፅ ያለው አባል አገር ውድቅ ማድረግ የለበትም)።
በመቀጠል በ193 አባል አገራት የጠቅላላ ጉባኤ መጽደቅ ይኖርበታል።
በአሁኑ ወቅት ለአንቶኒዮ ጉተሬዝ መንበር በዋናነት ከተጠቆሙት ዕጩዎች መካከል የቀድሞዋ የቺሊ ፕሬዚዳንት ሚሼል ባቼሌት እና የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ ይገኙበታል።
የትራምፕ ልዩ መልእክተኛ የሆኑት ፓኦሎ ዛምፖሊ ይህንን የትራምፕ ሀሳብ ሲደግፉ«እንደዚህ ያለ ድንቅ ሀሳብ ሊያመጣ የሚችለው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ብቻ ነው። በተመድ 193 አባል አገራትን ነው የሚያስተዳድሩት፤ በፊፋ ደግሞ ከ200 በላይ አባል ሀገራት አሉ፤ ኢንፋንቲኖ ድርጅቱን በብቃት የማስተዳደር ትልቅ ተሞክሮ አለው» ብለዋል።
ኢንፋንቲኖ ለዚህ የሥልጣን መንበር ፍላጎት እንዳላቸው ወይም ትራምፕ ጉዳዩን በቀጥታ ከእሳቸው ጋር ስለመወያየታቸው የተረጋገጠ ነገር የለም። የኋይት ሀውስ አካላትም እስካሁን በይፋ የሰጡት አስተያየት የለም።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
ዶናልድ ትራምፕ ጂያኒ ኢንፋንቲኖን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ማድረግ ይፈልጋሉ

More Stories
ዊሊያም ሳሊባ በጉዳት ምክንያት ለረዥም ጊዜ ከሜዳ ይርቃል
ጣሊያን ፔፕ ጓርዲዮላን ዋና አሰልጣኝ አድርጋ ለመሾም ንግግር ማድረግ ጀመረች
አርሰናል ብሩኖ ጊማሬሽን ለማስፈረም ከኒውካስል ጋር ቀጥታ ድርድር ጀምሯል!