ጣሊያን ፔፕ ጓርዲዮላን ዋና አሰልጣኝ አድርጋ ለመሾም ንግግር ማድረግ ጀመረች
ጣሊያን የቀድሞውን የማንቼስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላን የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርጋ ለመሾም ንግግር መጀመሯ ተረጋግጧል።
የቀድሞው የማንቼስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን (አዙሪ) ዋና አሰልጣኝ እንዲሆኑ ለማድረግ የጣሊያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን (FIGC) ውይይት ማድረጉን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ጆቫኒ ማላጎ አረጋግጠዋል።
የጣሊያን ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ባለስልጣን ጂዮቫኒ ማላጎ እንደገለፁት፤ፌዴሬሽኑ ጓርዲዮላን ወደ ጣሊያን ለማምጣት ልዩ የፋይናንስ ‘ልዩነቶችን’ ወይም የበጀት ማስተካከያዎችን ለማድረግ ዝግጁ ነው።
ፕሬዚዳንት ጆቫኒ ማላጎ ለጣሊያን ስፖርት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃል”የፋይናንስ ልዩ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፤ እነዚህ ልዩ ሁኔታዎች በዚህ ሰዓት በስፋት ስሙ እየተነሳ ላለው ፔፕ ጓርዲዮላ የሚመለከቱ ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ ማላጎ ገልጸዋል።
አያይዘውም “ምንም እንኳን ግልጽ በሆኑ ምክንያቶች ዝርዝሩን ባልገልጸውም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ከግብ ይደርሳል ማለት ግን አይቻልም” ብለዋል።
ማላጎ አክለው እንደገለጹት፤ ጓርዲዮላ ብቸኛው እጩ አይደለም። ጣሊያንን እ.ኤ.አ. በ2020 የአውሮፓ ሻምፒዮን ያደረጉት የቀድሞው አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ እና የቀድሞው የአዙሪ አማካኝ አንድሪያ ፒርሎም በዕጩነት ከተያዙት ስሞች መካከል ይገኙበታል።
ስፔናዊው ታላቅ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ከ10 ስኬታማ ዓመታት በኋላ በቅርቡ ከማንቼስተር ሲቲ ጋር መለያየታቸው ይታወሳል።
በዚህ የ10 ዓመታት ቆይታቸው 6 የፕሪሚየር ሊግ፣ 3 የኤፍኤ ካፕ፣ 5 የሊግ ካፕ እና 1 የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችለዋል።
ጣሊያን ለሶስተኛ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ሳትችል መቅረቷን ተከተሎ አሰልጣኝ ጄናሮ ጋቱሶ ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ከሃላፊነታቸው በመልቀቃቸው አዙሪዎቹ ያለ አሰልጣኝ ይገኛሉ።
ጓርዲዮላ ከዚህ ቀደም በጣሊያን በአሰልጣኝነት ሰርተው ባያውቁም በተጫዋችነት ዘመናቸው በብሬሺያ እና ሮማ ክለቦች ( እ.ኤ.አ ከ2001-2003) ያሳለፉ በመሆናቸው የሀገሪቱን ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩ ከመሆኑም በላይ ለጣሊያን እግር ኳስ ባህል እንግዳ አይደሉም።
ይህ ዝውውር ከተሳካ ጓርዲዮላ ከሃንጋሪያዊው ላጆስ ቼዝለር እና ከአርጀንቲናዊው ሄሌኒዮ ሄሬራ በመቀጠል በጣሊያን የእግር ኳስ ታሪክ ብሔራዊ ቡድኑን በመምራት ‘ሶስተኛው የውጭ ሀገር አሰልጣኝ’ ያደርጋቸዋል።
ከሲቲ ከተለያየ በኋላ «በጣም ደክሞኛል» ሲል የተናገሩት ጓርዲዮላ፣ የጣሊያንን ብሔራዊ ቡድን እንደ አዲስ ለመገንባት የሚያደርገው ጉዞ በቅርቡ እውን ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
አርሰናል ብሩኖ ጊማሬሽን ለማስፈረም ከኒውካስል ጋር ቀጥታ ድርድር ጀምሯል!
ፊል ፎደን በማንቸስተር ሲቲ ቤት ውሉን አራዘመ
ቼልሲ ሞርጋን ሮጀርስን በ117 ሚሊዮን ፓውንድ አስፈረመ