የክረምት ጊዜያቸውን ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ ባላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ማዋላቸው ደስታ እንደፈጠረላቸው የሆሳዕና ከተማ ወጣቶች ተናገሩ

የክረምት ጊዜያቸውን ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ ባላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ማዋላቸው ደስታ እንደፈጠረላቸው የሆሳዕና ከተማ ወጣቶች ተናገሩ

በከተማዋ በአረንጓዴ ልማት፣ በጽዳትና በሌሎች በርካታ ዘርፎች የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተጠቁሟል።

በሊች አምባ ቀበሌ በጽዳት ዘመቻና በችግኝ ተከላ ሲሳተፉ ያገኘናቸው ወጣቶች እንደገለጹት፥ ክረምቱን ለአካባቢያቸው ማህበረሰብ የሚጠቅሙ ስራዎች ላይ ማሳለፋቸው ነገ የተሻለች ሀገር ለመፍጠርና ጠንካራ ትውልድ ለመቅረጽ የሚያስችል ነው።

የወጣትነት ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም የጀመሩትን መልካም ስራ እስከ መጨረሻው እንደሚያስቀጥሉም ገልጸው፥ ሌሎች ወጣቶች ጊዜያቸውን በከንቱ ሳያባክኑ በመሰል የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የሊች አምባ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ አማኑኤል አበሞ በበኩላቸው፤ ወጣቶች የክረምት እረፍት ጊዜያቸውን ማህበረሰቡን በማገልገል እንዲያሳልፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የአረጋውያንን ቤቶች ማደስና መገንባት፣ በአረንጓዴ አሻራና በከተማ ጽዳት መሳተፍ፣ ለማጠናከሪያ ትምህርት (ቱቶሪያል) ድጋፍ ማድረግና በሌሎ ችም ዘርፎች ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ወጣቶቹ በሊች አምባ ጤና ጣቢያ ግቢ ውስጥ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ተከላና የጽዳት ዘመቻ ያካሄዱ ሲሆን፥ የጤና ጣቢያው ዳይሬክተር ሲስተር ሰብለ በየነ እንደተናገሩት፥ በተቋሙ ቅጥር ግቢ የተተከሉት የፍራፍሬ ችግኞች ለአካባቢው አየር ንብረት መሻሻል ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባሻገር የእናቶችና ህጻናትን አመጋገብ ለማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው።

አክለውም ጤና ጣቢያው በጎ ፍቃደኞችን በማሳተፍ በእናትና ህጻናት ጤና ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ለእናቶች ማቆያ ፕሮጀክት ግንባታ የሚውል “መቶ ብር ለእናቴ” የተሰኘ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኪበሞ ሰለሞን በበኩላቸው፤ በከተማዋ በሚቀጥሉት የክረምት ወራት በ15 የአገልግሎት ዘርፎች በሁሉም ቀበሌያት የበጎ ፈቃድ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።

“የዛሬው የችግኝ ተከላና የጽዳት ዘመቻ አካባቢውን ውብና ማራኪ ከማድረግ ባሻገር አየር ንብረቱን በመጠበቅ ረገድ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው” ያሉት አቶ ኪበሞ፤ በከተማ ደረጃ ከ3 ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር መገበቱን አስረድተዋል።

በዕለቱ በሊች አምባ ጤና ጣቢያ በተደረገው ጉብኝትና የተከላ መርኃ- ግብር ላይ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባዔ ወ/ሮ ሙሉነሽ ሴዲሶን ጨምሮ የከተማና የቀበሌ አመራሮች፣ ወጣቶች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን