ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በተሰረው ስራ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በተሰረው ስራ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በተሰረው ስራ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን በስልጤ ዞን የምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ መንገድ ትራንስፖርት ጽ/ቤት አስታወቀ።

በዘንድሮ የበጀት ዓመት ከህብረተሰቡ ከ62.5 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ በወረዳው በ19 መንደሮች ከ84.5 ኪ.ሜ በላይ የከፈታ ስራዎችና ሌሎችም የመሠረተ ልማት ተግባራት መከናወናቸው ተመላክቷል።

የምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ዋና ሀላፊ አቶ ሙባሪክ ሀሰን እንደገለጹት በበጀት አመቱ የወረዳው ማህበረሰብ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በተሰረው ስራ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፥ በዚህ አመት በወረዳው በ19 መንደሮች በተሰራው መንገድ ከፈታ ከ84.5 ኪ.ሜትር በላይ የሚሆን የመንገድ ስራ የተሰራ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 19.5 ኪ.ሜትሩን ጠጠር ማልበስ በመቻሉ በርካታ የማህበረሰቡን አካላት ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ አመላክተዋል።

በ2018 የበጀት ዓመት መንግስትና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ የገለፁት አቶ ሙባሪክ በተለይም ለረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ የቆየው የእመዣር-ጋሮሬ- እና በወረዳው በታች ዑምናን ቀበሌ የሚገኘውን የሓጅ አሊዬ መስጂድና መካነ-መቃብር ለማልማት ከጎሞሮ ወደ ስፍራው የሚወስደውን መንገድ እና የድልድይ ስራ መስራት የተቻለ መሆኑ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋፋት እንደ ወረዳው ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ የመንገድ ስራ ስትራክቸሮችን፣በተለያዩ ቀበሌያት ደብል እና ሲንግል ፓይፕ ድልድዮችን መስራት ተችሏል ያሉት ኃላፊው ለዚህም ወረዳው ቀደም ብሎ ለመንገድ ስራ የገዛቸውና የሚጠቀምባቸው የመንገድ ማሽነሪዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

የወረዳው መልከዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ለመንገድ ስራው አመቺ ያለመሆኑን ያነሱት ኃላፊው ይህም ሆኖ በበጀት አመቱ በዞኑ ተሞክሮ የሚሆን ስራ ተሰርቷል፤ ለዚህ ውጤታማ ተግባር ደግሞ የወረዳው ማህበረሰብ ከ62.5 ሚሊየን በላይ ብር በማሰባሰብ እና ጉልበቱንና ጊዜውን በመለገስ ከመንግስት ጎን ሆኖ ያደረገው ርብርብ ጉልህ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል።

በወረዳው አዳዘር ሼበል ቀበሌ የስሪር መንደር እና ሌሎችም መንደሮች ላይ መንገድ የመክፈት ስራ ተሰርቶም ለተሽከርካሪ የመሬቱ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ አመቺ እንዳልሆነ ያነሱት ኃላፊው በቀጣይ ጽ/ቤቱና የወረዳው አስተዳደር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

በወረዳው በተለያዩ ቀበሌያት አግኝተን ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ ባርሰንጋ አብዲ እና ወ/ሮ ሽፍቴ ኑሩ በበኩላቸው በመንገድ ከፈታ ስራው በብዙ ነገሮች ተጠቃሚ በመሆናቸው ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ ጠጠር ያልለበሱ መንገዶችን በማጠናቀቅ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ ወረዳው ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ: ሃጀራ ግርማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን