ትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አሊ አህመድ አዲስ አበባ ገባ

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አሊ አህመድ አዲስ አበባ ገባ

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አሊ አህመድ በኢትዮጵያ ቆይታ ለማድረግ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብቷል።

አሊ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ ሲደርስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አበበ አማረ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሮቶኮል ዲፓርትመንት እና የመጽሐፍ ኒስቴር መስሪያ ቤት ተወካዮች አቀባበል ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አሳውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር እና የኢትዮጽያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አሊ አህመድ በኢትዮጵያ የሚያደርገው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን የጋራ ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በእንግሊዙ ኖርዊች ሲቲ እየተጫወተ የሚገኘውና በ2026 የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን በአራት ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈው አሊ አህመድ እስከ ዓለም ዋንጫ ተሳትፎ የደረሰው የእግር ኳስ ጉዞው እና ስኬቶቹ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከፍተኛ ተነሳሽነት የሚፈጥር መሆኑ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዓለም ዙርያ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውን የሀገራቸውን መለያ ለብሰው እንዲጫወቱ ላለፉት ጊዜያት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ የሚገኝ መሆኑን ገልፆ አሊ አህመድ ምንም እንኳ በሌላ ብሔራዊ ቡድን ማልያ እየተጫወተ ቢሆንም አሁንም ኢትዮጵያን መወከል የሚችሉ ተሰጥኦዎች በመላው ዓለም እንደሚገኙ ትልቅ ማሳያ መሆኑ ተመላክቷል።

ፌዴሬሽኑ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር ቁርኝች ለመፍጠር ለሚያደርገው ጥረት እና ለቀጣይ አጋርነቶች የአሊ አህመድ አዲስ አበባ መምጣት ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልጿል።

ዘጋቢ ፡ሙሉቀን ባሳ