በታሪካዊው ምስል የተገናኙት ሜሲ እና ያማል፤ በዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ፊት ለፊት!
በእግር ኳሱ ዓለም ከልብ ወለድ ድርሰቶች ይልቅ እውነተኛው የእጣ ፈንታ መስመር እጅግ የሚያስገርሙ ታሪኮችን ይፅፋል።
የዓለማችን የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ እና የባርሴሎናው አዲሱ ኮከብ ላሚን ያማል በዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ ሀገሮቻቸውን አርጀንቲና እና እስፔንን ወክለው ሊፋለሙ ቀጠሮ ይዘዋል።
የ39 ዓመቱ አርበኛ እና የ19 ዓመቱ ታዳጊ በዓለማችን ትልቁ የስፖርት መድረክ ላይ ፊት ለፊት ለመገናኘት መብቃታቸው የሜሲን የማይበገር ፅናት እና የያማልን ልዩ የወደፊት ተስፋ የሚያሳይ ነው።
ነገር ግን የሁለቱ ተጫዋቾች የቅርብ ታሪክ የጀመረው ዛሬ አይደለም፤ የዛሬ 19 ዓመት ገደማ በካምፕ ኑ ስታዲየም መልበሻ ክፍል ውስጥ ነበር።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2007 ገና የ20 ዓመት ወጣት የነበረው ሊዮኔል ሜሲ በባርሴሎና ዋና ቡድን ውስጥ ቦታውን እያጠናከረ ነበር።
በወቅቱ ገና የ5 ወር ህፃን የነበረው ያማል ቤተሰቦች ደግሞ በ’ስፖርት’ ጋዜጣ እና በዩኒሴፍ (UNICEF) አዘጋጅነት የቀረበን የእጣ ውድድር ያሸንፋሉ።
እጣው ለተመረጡ ህፃናት ከባርሴሎና ተጫዋቾች ጋር የፎቶ መታሰቢያ የመቅረፅ ዕድል የሚሰጥ ነበር። በዕጣው አጋጣሚ ታዳጊው ያማል ከሜሲ ጋር ይገናኛል።
ፎቶውን ያነሳው የ58 ዓመቱ ካታላናዊ ፎቶግራፈር ጆአን ሞንፎርት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ”ሜሲ በጣም አይናፋር እና የተረረጋጋ ሰው ነው። ወደ መልበሻ ክፍል ገብቶ ድንገት ከታዳጊ ህፃን ጋር ፎቶ እንዲነሳ ሲነገረው ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ተጋብቶ ነበር! ነገር ግን ያማል በጣም ደስተኛ እና ፈገግተኛ ህፃን ስለነበር፤ ሜሲም በፍጥነት ከሁኔታው ጋር ተላመደ ሲል” ይናገራል።
በወቅቱ ተቀርፀው የነበሩት ምስሎች ለዓመታት ተረስተው የቆዩ ቢሆንም፤ በ2024 ያማል እስፔንን በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊነት ሲያበቃ የያማል አባት ምስሉን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ “የሁለት ታላላቅ ኮከቦች ጅምር” በሚል መግለጫ አጋርተውት ነበር።
ፎቶግራፈሩ ሞንፎርት ይህን ሁኔታ “በፊልም እንኳ ብትፅፈው አያምኑህም፤ እውነተኛ የእጣ ፈንታ ተአምር ነው” ሲል ገልፆታል።
የላሚን ያማል ታሪክ የችሎታ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ መስዋዕትነት ውጤት ነው። ከሞሮኮ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ የተፈናቀሉ ቤተሰቦቹ በባርሴሎና አቅራቢያ በምትገኘው ሮካፎንዳ በተባለች የስደተኞች መንደር ውስጥ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ይኖሩ ነበር።
ያማል ሙሉ ስሙ ላሚን ያማል ናስራዊ ኤባና ሲሆን፤ “ያማል” የሚለው የስሙ አካል የቤተሰቡን የቤት ኪራይ እና ወጪዎች ይሸፍኑ ለነበሩ ሁለት የቅርብ ወዳጆች እንደ ምስጋና የተሰጠ ስም ነው።
“ላሚን” ማለት ታማኝ፣ “ያማል” ማለት ደግሞ ውበት ወይም ውበት ያለው ማለት ነው።
ያማል በጨዋታዎች ላይ ግብ ሲያስቆጥር በእጆቹ የ “3-0-4” ምልክት በማሳየት ያደገበትን የሮካፎንዳ መንደር ፖስታ ኮድ (08304) ዘወትር ያከብራል።
ያማል ስለ ቤተሰቡ ሲናገር “እናትና አባቴ ለእኔ ያደረጉትን እኔ ለማንም ማድረግ የምችለው አይመስለኝም። ገንዘብ በሌለበት ሁኔታ ልጅህ እግር ኳስ እንዲጫወት ማድረግ እጅግ ከባድ ነው። እነሱ ግን ይህን እውን አድርገውታል። ውለታቸውን በጭራሽ መክፈል አልችልም” ሲል ተናግሯል።
በ19 ዓመቱ ሜሲ 11 ግቦችን አስቆጥሮ አንድ የላሊጋ እና አንድ የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አንስቶ የነበረ ሲሆን፤ ያማል በተመሳሳይ እድሜው 56 ግቦችን በማስቆጠር 3 የላሊጋ፣ 1 የኮፓ ዴልሬይ እና 1 የአውሮፓ 20 ዋንጫን በማንሳት ድንቅ አቅሙን አሳይቷል።
አሁን ደግሞ ከ19 ዓመታት በኋላ፣ በፎቶግራፉ ላይ ታቅፎ የነበረው ህፃን እና አቃፊው ወጣት በዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ ሀገሮቻቸውን ወክለው በስተቀኝ ክንፍ መስመር ላይ ፊት ለፊት ይገናኛሉ።
የሁለቱን የመጀመርያ ታሪክ በካሜራው ያስቀረው ፎቶግራፈር ሞንፎርት ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ ሲያጠቃልል”የታሪካቸው ዑደት እየተዘጋ ይመስለኛል። እኔ የባርሴሎና ደጋፊ ነኝ፤ ለሜሲ ሁለተኛውን የዓለም ዋንጫ አሸንፎ በክብር ቢሰናበት ደስ ይለኛል፤ ይገባዋል።
በሌላ በኩል ያማል ገና ረጅም ጊዜ አለው፤ ነገር ግን አሁን ካለበት ብቃት አንፃር ዋንጫውን ካሸነፈ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል። እውነት ለመናገር ልቤ ለሁለት ተከፍሏል” በማለት ተናግሯል።
የእግር ኳስ አፍቃሪው ዓለም አሁን የዚህን “የእጣ ፈንታ ተአምር” የመጨረሻ ምዕራፍ ለመመልከት በጉጉት እያሰፈሰፈ ይገኛል።
በሁለቱ ተጫዋቾች ሀገራት አርጄንቲና እና ስፔን መካከል የሚካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ የፊታችን እሁድ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
አርሰናል ክርስቶስ ዞሊስን ለማስፈረም ተስማማ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በወልቂጤ ከተማ የሰርከስ ስፖርት ምልመላና የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት መርሃ ግብር ተካሄደ
አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል እንግሊዝ ወደ ፍፃሜ ባለማለፏ ከፍተኛ ትችትን አስተናገዱ