ያለፈውን በጀት ዓመት ተግባራት በፖሊስ ተቋምና በግለሰቦች ደረጃ በመገምገም ቀጣይ የስራ አቅጣጫን መለየት እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መስከረም 05/2019 ዓ.ም(ደሬቴድ) ያለፈውን በጀት ዓመት ተግባራት በተቋምና በግለሰቦች ደረጃ በመገምገም ቀጣይ የስራ አቅጣጫን መለየት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ አሳሰቡ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም በቦንጋ ከተማ እየተገመገመ ነው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ 2018 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ የተደረገበት መሆኑን አስታውሰው፤ የግምገማ መድረኩም ምርጫው በስኬት ተጠናቆ የመንግስት ምስረታ የሚደረግበት ወቅት ላይ መካሄዱ ለየት የሚያደርገው ነው ብለዋል።
የህዝብ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለማስቻል በሚደረገው ጥረት ላይ ተቋሙ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመላክተዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት ተግባራት የተከናወኑበትን እና ውጤት የተገኘበትን ሁኔታ በተቋምና በግለሰቦች ደረጃ በመገምገም ቀጣይ የስራ አቅጣጫን መለየት እንዲሁም እውቅና መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተመሣሣይ ሁኔታ ያልተሳኩ ተግባራትንና ምክንያቶቻቸውን መለየትና መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በወንጀል መከላከል የህዝብ አደረጃጀትን በመጠቀም እንዲሁም በወንጀል ምርመራና በአስተዳደር ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትን ከወቅቱ ሁኔታና መሬት ላይ ካሉ እውነታዎች ጋር በማያያዝ ግምገማ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ለሚቀጥለው ጊዜ የሚመጥን አቋም ያለው ተቋምንና የፖሊስ ሠራዊት አባላትን መፍጠር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ካሣ እንደተናገሩት፤ መድረኩ ባለፈው በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራት ተገምግመው ችግሮች እንዲስተካከሉ እና ውጤታማ ተግባራት እንዲቀጥሉ አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነው ብለዋል።
የኮሚሽኑ ተግባራት በተለያዩ መዋቅሮች ደረጃ በተሰሩበት ሁኔታና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ ግምገማ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም የሚያመላክት ሰነድ እየቀረበ ሲሆን፤ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና የዞኖች ፖሊስ መምሪያ አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን፤ የሂስ ግለሂስ እንደሚደረግም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓልን ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
ጦርነቱ ሳዉዲ አረቢያ እና ሁቲ በከፈቱት የተኩስ ልውውጥ እንደ አዲስ አገርሽቷል
የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ በሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት የማህበረሰቡ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል እያከናወነ የሚገኘውን አበረታች ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለፁ